በድሬዳዋ የወረዳ ሁለት የባርጌሌ ሰፈር ነዋሪዎች
የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የህብረተሰብ ተሳትፎ ኤጀንሲ ከወረዳ ሁለት ጋር በመተባበር በባርጌሌ መንደር ያስገነባው የ 1 ኪሎ ሜትር የውሃ መውረጃ ዲች እና የ 7 መቶ ሜትር የጠጠር መንገድ ስራ ፕሮጀክት ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በድምቀት ተመርቋል።
በዚህም በምርቃት መርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ለአካባቢው ማህበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤ ከለውጡ አመታት ወዲህ በድሬዳዋ አስተዳደር የማህበረሰቡን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በቀጣይም ማህበረሰቡን ያሳተፉ ፕሮጀክቶችን በየወረዳው የማከናወኑ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመላከቱት አቶ ኢብራሂም ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአስተዳደሩ ህብረተሰብ ተሳትፎ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ወ/ሮ ረሂማ አወል በበኩላቸው ከማህበረሰቡ ጋር በመወያየት አንገብጋቢ ችግሮች ተለይተው ወደ ስራ መገባቱን የገለፁ ሲሆን በፕሮጀክቱም የ1 ሺ ሜትር የውሃ መውረጃ ዲች እንዲሁም የ7 መቶ ሜትር የጠጠር መንገድ እና በአካባቢው የነበረውን ሀዲድ በማንሳት ጫካ የመመንጠር ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።
ወ/ሮ ረሂማ አያይዘውም የፕሮጀክቱ ስራ ከመከናወኑ በፊት አካባቢው ለኑሮ ምቹ ያልነበረ በዝናብ ወቅት ውሃ በማቆር በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከት የነበረ መሆኑን አስታውሰው አሁን ላይ ግን በፕሮጀክቱ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በጥራት እና በፍጥነት በተሰሩ ስራዎች ችግሮቹ መቀረፋቸውን ጠቁመዋል።
የወረዳ 2 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ከህብረተሰቡ ችግር ተነስተው መፍትሄ እየሰጡ የሚገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
ለበርካታ አመታት በአቧራ እንዲሁም በጭቃ እና በጎርፍ ሲማረሩ እንደቆዩ የገለፁት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ አሁን ላይ ችግራቸው ተሰሚነት አግኝቶ በመቀረፉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።


