የትራንስፖርት ዘርፍን በማዘመን ከነዳጅ ወጪ በማዳን በከፍተኛ ጥራት የተመረቱ 2025 ሞዴል የሆኑ ተሸከርካሪዎችን ወደ ከተማችን በማስገባት የሚታወቀው ስዊፍት ህብረት ስራ ማህበር በኤሌትሪክ ቻርጅ የሚሰሩ 200 ተሸከርካሪዎችን ለአገልግሎት አቅርቧል፡፡
በቁልፍ ርክክብ ስነስርአቱ ላይ ተገኝተው የተሸከርካሪዎቹን ሰሌዳና ቁልፍ ለአባላቱ ያስረከቡት ክቡር አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በድሬዳዋ አስተዳደር የብልፅግና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡
ኃላፊው በመልዕክታቸው የገቡትን ቃል ወደ ተግባር በመለወጥ ይህንን ከትራንስፖርት በዘለለ ለአስተዳደሩ ነዋሪዎች የስራ እድል የፈጠረ፣ የአካባቢ ብክለትን የሚቀንስ፣ የቁጠባ ባህልን የሚጨምር ፣ የነዳጅ ወጪን በመቀነስ ለኢኮኖሚ ወሳኝ ሚናን የሚጫወት ዘመናዊ ትራንስፖርት ወደ አስተዳደራችን በማስገባት ሂደት ጉልህ ሚና ያላቸውን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም የዚህ አይነቱ ተግባር ሊስፋፋ የሚገባ መሆኑን ጠቁመው ፤ የዛሬ የእድሉ ተጠቃሚዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሹክሪ አብዱረህማን በበኩላቸው ስዊፍት የቀድሞ ተሸከርካሪዎችን በመተካት በተለይም መነሻቸውን ከኤርፖርት አድርገው ከተማዋን በታክሲ እያገለገሉ ያሉ ፔጆዎችን በመተካት እንዲሁም በኮሪደር ልማት በተሰሩ መንገዶች ላይ በቀጣይ የታክሲ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
የስዊፍት ትራንስፖርት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ አሸብር የትራንስፖርት ዘርፉ ይበልጥ እንዲዘምንና ከተማዋን ሊመጥን የሚችል ፣ ከነዳጅ ወጪ ጫና እስከ አካባቢ ብክለት ያለን ተፅዕኖ የሚቀርፉ ጥራታቸው የተመሰከረላቸው ለአጠቃቀም ቀላልና ምቹ መኪኖችን በተመጣጣኝ ዋጋ በአምስት አመት ክፍያ አብዛኛው የአስተዳደሩን ነዋሪዎች እምነት ከግምት በማስገባት ከወለድ ነፃ በሆነ አማራጭም ጭምር ይዘው መቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቃልን በተግባር በሚል መርህ የአባላትን የፋይናንስ አቅም በማጠናከር ተጠቃሚ የሚያደርግና አገሪቱንም በነዳጅ ወጪ ከውጪ አገራት የኢኮኖሚ ተፅእኖ የሚያድን ይሄ የህብረት ስራ ማህበር ከትራንስፖርት ዘርፍ በዘለለ የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ለቤት፣ ለትምህርት፣ለንግድ፣ ለጤና እንዲሁም ለማህበራዊ ጉዳዮች የሚሆን ብድርን በማመቻቸት ለአገልግሎት ማቅረቡን አቶ ብሩክ አስታውቀዋል፡፡
ተሸከርካሪዎቹን ከተረከቡ አባላት መካከል ያነጋገርናቸው የዛሬ ተጠቃሚዎች እንደገለፁት የዚህ አይነቱ ብድር ስርአት መዘርጋቱ ቁጠባን ባህል ለማድረግ ከማስቻሉ በዘለለ በአነስተኛ ወለድ በጥቂት አመታት ውስጥ የመኪና ባለቤት ለመሆን በማስቻሉ ደስታቸው ወደር እንደሌለው ገልፀው፤ የስዊፍት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላ/የተ/ህ/ስ/ማህበርን ቃሉን በተግባር ስለተገበረ አመስግነዋል፡፡


