የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ንቅናቄ የቤተሰብ ኃላፊነት እና የማህበረሰብ አጋርነት አደረጃጀት ዝርጋታ ላይ ከከተማ ወረዳዎች አመራሮች ጋር እንዲሁም ከማህበረሰቡ ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው ዕለት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እና የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እንደ ሀገር የተጀመረውን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ኢንሼቲቭ ውጤታማነት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤በንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ23.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ከእርዳታ እንዲወጡ የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
አቶ ሻኪር አያይዘውም እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን በማዳበር ከተረጂነት መላቀቅ እንደሚገባ እንዲሁም ተረጂነትን የሚጠየፍ አይበገሬ ማህበረሰብ ለመፍጠር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
አስቸኳይ የሆኑ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚገጥሙበት ጊዜ ማህበረሰቡ ችግር ውስጥ ሳይገባ ችግሩን ተቋቁሞ ማሳለፍ እንዲችል ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሻኪር ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር አቶ ሱሌማን አሊ በበኩላቸው ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም በሚል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት የተረጂነት አስተሳሰብንና ተግባርን የሚያስቀሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን ለማጠናከር ከአመራሩ እና ከማህበረሰቡ የተውጣጣ የአይበገሬነት አብይ ኮሚቴ ተደራጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባ አቶ ሱሌማን ገልፀው፤ ኮሚቴ ማህበረሰቡ ከጠባቂነት ተላቆ ወደ አምራችነት እና ወደ ብልፅግና እንዲቀየር የማስቻል ስራዎችን በስፋት እንደሚሰራ አብራርተዋል።


