የድሬዳዋ አስተዳደር የፀጥታ ግብር ሀይል እንዳስታወቀዉ በድሬዳዋ ፣በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የሆኑ ተጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎችን መሽሸጊያ በማድረግ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ልማትን ለማደናቀፍ ሙከራ ሲያደርግ የነበረው የሸኔ የሽብር ቡድን ላይ ባፉት ቀናት ጥምር የፀጥታ ሀይሉ ባካሄደዉ የጋራ ስምሪትና በወሰደዉ ጠንካራ እርምጃ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸዉን አስታውቋል::
ይሄዉ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ሃይል ማለትም የሀገር መከላኪያ ሰራዊት ምስራቅ ምድብ ፣የፌደራል ፖሊሰ ምስራቅ ምድብ ፈጥኖ ደራሽ ፣የኦሮሚያ ምስራቅ ሀረርጌ ፖሊስና ሚኒሻ ፣የሱማሌ ክልል ፖሊስ፣ ማያ ሲቲ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል መከላከልና የድሬዳዋ አስተዳደር የሚኒሻ ሀይል በጥምረት በወሰዱት የጋራ እርምጃ 22 የሸኔ ሽብር ቡድን አባላት ሲደመሰሱ 6ቱ እጅ የሰጡ ሲሆን የጥፋት ቡድኑ ይጠቀምባቸዉ የነበሩ 24 ክላሽ ኢንኮቭ እና 1 ስናይፐር ፣ 23 የወገብ ትጥቆች እንዲሁም ፣የእጅ ቦንብ ፣ሶላር ፣ብትን ጥይት የጦር መሣሪያዎች መማረካቸውን በመግለጫዉ አስታውቋል::
ከእዚሁ ጋር ተያይዞ ለሽብር ቡድኑ የጥፋት ተግባር ማስፈፀሚያ የተለያዩ ግለሰቦችና አካላትን በማገትና በማስገደድ ገንዘቦችን የተቀበሉና በባንክ ሂሳብ ቁጥራቸዉ ሲያስተላልፉና ሲያዘዋዉሩ የነበሩ እንዲሁም ከሽብር ቡድኑ ጋር ግንኙነት የነበራቸዉ ሌሎች አካላት በፌደራል ፖሊስ ምስራቅ ምድብ ምርመራ ዲቪዠን፣ በድሬዳዋ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍና የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ፖሊስ የጋራ ጥምረት በቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራቸዉ እየተጣራ እንደሚገኝ የፀጥታ ግብረ ሀይሉ በመግለጫዉ አስታዉቋል;;
የፀጥታ ጥምር ሀይሉ ባወጣዉ በእዚሁ መግለጫ በሸኔ የሽብር ቡድኑ ላይ የፀጥታ ጥምር ሀይሉ በወሰደዉ የተቀናጀ እርምጃ ከፍተኛ ቁሳዊና ሰብዓዊ ኪሳራ በሽብር ቡድኑ ላይ ደርሶል ያለ ሲሆን በሽብር ቡድኑ ላይ የተወሰደዉን እመርጃ ጨምሮ የፀጥታ ሀይሉ ሰላምና ፀጥታን በአስተመማኝ ደረጃ ለማረጋገጥ ባካሄዳቸዉ ስምሪትና ተግባራት ሁሉ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠትና ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን ላደረገዉ እና እያደረገ ላለዉ ከፍተኛ አስተዋፆና ድጋፍ የፀጥታ ግብረ ሀይሉ ምስጋናዉን አቅርቧል::
ግብረ ሀይሉ በመግለጫዉ ማጠቃለያም የምስራቅ ኢትዮጽያ የፀጥታ ጥምር ሀይል በጋራ በሽብር ቡድኑ ላይ በወሰዳቸዉ የተጠናከሩ እርምጃዎች አሁን ላይ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸዉን እና አካባቢዉን ከሽብር ቡድኑ ነፃ ማድረግ መቻሉን ገልፆ አጠቃላይ ሁኔታዉን የተመለከተ መግለጫ በዝርዝር በቀጣይ እንደሚሰጥም የፀጥታ ግብረ ሀይሉ ጨምሮ አስታዉቋል::


