የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከ UN Habitat እና የድሬዳዋ አሰተዳደር የከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ጋር በመተባበር በከተማ ፅዳት እና ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መድረክ አዘጋጀ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ፅዳት እና ቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ከ UN Habitat እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ስራ አስኪያጅ ጋር በመተባበር የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እንደሚሰራ ተጠቆመ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባለ ድርሻ ካላትን ያሳተፈ የአንድ ቀን የምክክር መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን የአስተዳደሩን ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተወካይ ጨምሮ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እና ምሁራን፣ የከተማ ነዋሪዎች እና በፅዳት ሰራ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል እንደተናገሩት ‘’ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ምቹ እና ፅዱ የከተማ ገፅታ እንዲፈጠር ከማስቻሉም በላይ የአየር ብክለት እና ተዛማጅ አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ ሚና የኖረዋል’’ ብለዋል::

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እና ማህበርሰብ አቀፍ የልማት ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ተማም የድሬዳዋ ከተማን ፅዱ እና ለመኖሪያ ምቹ በማድረግ ሂደት ውስጥ ከ UN Habitat ጋር የተጀመረው ፕሮጀከት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ UN Habitat ተወካይ አቶ ፍፁም ፀጋዬ በአስተዳደሩ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና የድሬዳዋ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ጋር በትብብር ስለሚሰራዉ የቁሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀከት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፣ ደ/ር ዮናስ ታደሰ ከደሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ዶ/ር ሴሎ ዝባግዌ ከ UN Habitat እና አቶ ጌታሁን ሽፈራው ከከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት በቁሻሻ አወጋገድ እና የከተማ ፅዳት ስራዎች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

የቀረቡትን ፅሁፎች ተከትሎ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ መርሃ ግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *