የድሬዳዋ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በአገልግሎት ዘርፍ የካይዘን ትግበራ የልምድ ልውውጥና የጋራ መግባቢያ ስምምነት መፈራረሚያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።
በመድረኩ የጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ግዛው እንደገለፁት በአስተዳደሩ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የካይዘን ትግበራ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ አመራሩ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተለይም የለውጥስራና መልካም አስተዳደር ዘርፍ ላይ የሚገኙ አመራሮች ውስጣዊ የአሰራር ስርዓትና የሃብት ብክነት ከመከላከል አንፃር ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እንደሚያስችል በተረዳ መልኩ የካይዘን አመራር ፍልስፍናን መተግበር እንዳለባቸው አቶ ግርማ ጠቁመዋል።
ኃላፊው አያይዘው ተቋማት የተመደበላቸውን ኃብት በውጤታማነት በመጠቀም ለተገልጋዮቻቸው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ በየተቋሙ የተጀመሩ የካይዘን ትግበራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የአመራር ክትትልና ድጋፍ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል አመራሩ ተቋምንና ስራዎችን በዲሲፒሊን አለመምራት የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ውጤታማ እንዳይሆን ከሚያደርጉ ጉዳዮቸ አንዱ መሆኑን ፣ ካይዘን በዘመቻ መልክ ብቻ ሳይሆን በመደበኛ የእለት ከእለት ስራዎች ጋር አስተሳስሮ መተግበር እንደሚገባ በብልፅግና ፖርቲ ድሬዳዋ የቅ/ፅ/ቤት ሃላፊ ልዩ ረዳት አቶ ዮናስ ጥግነህ አሳስበዋል።
በቀጣይም የካይዘን አተገባበር ያለበት ደረጃ ፓርቲው በተለያዩ መንገዶች በተቋማት በሚያደርጋቸው የክትትልና ግምገማ ሂደቶች አንዱ መመዘኛ ሆኖ እንደሚቀርብ አቶ ዮናስ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በካይዘን ስራ አመራር ትግበራ ረገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አቶ ወንድምአገኝ በሻህ በብልፅግና ፖርቲ የአቅም ግንባታ ዳሬክተር ተናግረዋል።
የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና በተቀመጠው የአገልግሎት ስታንዳርድ መሠረት ለመስጠት እንዲያስችል የካይዘን አፈፃፀምን ትግበራ በየግዜው ማየት እንደሚገባ ዳይሬክተሩ የገለፁ ሲሆን ካይዘንን ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር በተቋማት የካይዘን ግንዛቤና ማስጨበጫና ትግበራ ሂደቱን በማዳበር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ከተሳታፊዎች ውይይትና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን የካይዘን ትግበራን ለማጠናከር ከአመራር ጀምሮ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኛ በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚገባ በሰፊው ተነስቷል።


