በድሬዳዋ አስተዳደር ሴክተር ተቋማት በወረዳ 1 ገንደ ሁርሶ ገንደ ርጌ , በወረዳ 4 ገንደ ሎኒ እና ካባ እንዲሁም በወረዳ 7 ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ያስገነቧቸውን ሰባት የአባውራ መኖሪያ ቤቶች ከነሙሉ የቤት እቃው አስረከበ፡፡
የመኖሪያ ቤቶቹን ርክክብ መርሀ-ግብር ላይ መልእክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ ኢብራሂም ይሱፍ ለውጡን ተከትሎ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በየአመቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጋ ተኮር የሆኑ አገልግሎቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው ለአቅመ ደካሞች እና አረጋዊያን, በበጎ ተግባራት የሚከናወኑ ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት አካል መሆን ችለዋል ብለዋል።
እንደ ሀገር ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም ሆነ ሌሎች የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ ለአግልግሎት እንዲውሉ ከማድረግ ጎን ለጎንም መንግስት የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የሚያደርገው ይህ ዓይነቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሕዝባችን ያለንን አጋርነት የምንገልጽበት አንዱ ማሳያ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ኢብራሂም በቀጣይ ጠንክሮ በመሥራት፣ በመተጋገዝና ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ የሥራ ባህልን በማውረስ ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በቤት እድሳት መርሀ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑ አረጋዊያን እና አቅመ ደካማ ቤተሰቦች በበኩላቸው አስተዳደሩ አቅማችን በደከመ ጊዜ ቤት ገንብቶ ስላስረከበን ምስጋና እና አክብሮት ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


