የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ
በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በክረምት በጎ ፍቃድ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ በወረዳ 05፣ 08 እና 02 የተገነቡ ከ14 በላይ የሚሆኑ ቤቶችን መርቀው ቁልፉን ለባለቤቶቹ አስረክበዋል።
በአስተዳደሩ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች የአቅመ ደካማ ወገኖችን ችግር በተጨባጭ የቀረፉ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ምክትል ከንቲባው ገልፀው፤ በ2017 ዓ.ም 291 ቤቶችን በአዲስ መልክ ለመገንባት ታቅዶ 280 ቤቶችን ማጠናቀቅ እንደተቻለ እንዲሁም ከመቶ በላይ የሚሆኑ ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ ከ158 በላይ የሚሆኑ ቤቶችን ማደስ መቻሉን አብራርተዋል።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ አያይዘውም በርካታ ቤቶች ተገንብተው ቢጠናቀቁም በዛሬው ዕለት ወካይ የሆኑ ከ14 ቤቶች በላይ ተመርቀው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ማስረከብ መቻሉን የጠቆሙ ሲሆን በቀጣይ ከህዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ቀሪዎቹ ቤቶች ተጠናቀው እንደሚመረቁ አመላክተዋል።
ቤቶቹ በተለያዩ ተቋማት እና ባለሀብቶች ርብርብ መገንባታቸውን የገለፁት ምክትል ከንቲባው በቀጣይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች የሚያግዙ ተግባራት በስፋት ተጠናክረው መከናወን ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተለይም በወረዳ 05 ባልተገባ መልኩ የመንግስትን መሬት ሊወስዱ የነበሩ አካላትን ወረዳው በህግ አግባብ በማስለቀቅ ቦታው ላይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ቤት ሰርቶ ማስረከቡን ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ጠቁመው ይህም በአርዓያነት የሚወሰድ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት የቤቶችን ግንባታ አጠናቀው ካስመረቁ ተቋማት መካከል ሳቢያን ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ወረዳ 05፣ ስራ ክህሎት ቢሮ፣ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት እንዲሁም የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ይጠቀሳሉ።
ቤቶቹን የተረከቡት ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው፤ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


