በድሬዳዋ አስተዳደር የቤት ግንባታ የተከናወነላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች
በድሬዳዋ አስተዳደር በዛሬው ዕለት በክረምት በጎ ፍቃድ በወረዳ 05፣ 08 እና 02 የተገነቡ ከ14 በላይ የሚሆኑ ቤቶች በድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ እና በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ በክብርት ወ/ሮ ከሪማ አሊ ተመርቀዋል።
በዚህም የቤት ግንባታ ከተደረገላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች መካከል የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አለም መገርሳ ከዚህ ቀደም የምኖርበት ቤት የፋራረሰ ዝናብና ፀሀይ የሚያስገባ በመሆኑ ብዙ ችግር ደርሶብኛል በማለት ይናገራሉ።
ወ/ሮ አለም ሲያክሉም ቤታቸው በአዲስ ከመገንባቱ በፊት በተለይም በክረምቱ የሚወርደው ዝናብ ቤታቸው ውስጥ ያንጠባጥብ ስለነበር ተኝቶ ለማደር አስቸጋሪ መሆኑን አስታውሰው ፤ አሁን ላይ ቤታቸው በመገንባቱ “ከዚህ በኋላ ተኝቼ ነው የማድረው እንቅልፍ አልባ ለሊቶቼ አብቅተዋል” በማለት ደስታቸውን ገልፀዋል።
ከወ/ሮ አለም በተጨማሪም በወረዳ 05፣ 08 እና 02 የቤት ግንባታ የተከናወነላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች አዲስ ቤት ሳይገነባላቸው በፊት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ተናግረው፤ አሁን ላይ ዘመናዊ እና አዲስ ቤት በአስተዳደሩ እና በባለ ሀብቶች ድጋፍ ስለተገነባላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
በቤት ምርቃት መርሃ ግብሩ የአስቤዛ ድጋፍም ተበርክቶላቸዋል።


