የዳዊት ለአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከሉ ያስገነባው የአረጋውያን ባለ አንድ ወለል ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ ተመረቀ

የዳዊት ለአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከሉ ያስገነባው የአረጋውያን ባለ አንድ ወለል ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመረቀ።

የዳዊት ለአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር በ1998 ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ ደጋፊና ጧሪ የሌላቸውን ችግረኛ አረጋዊያንን እያገለገለ የሚገኝ በጎ አድራጎት ማህበር ነዉ ።

ማህበሩ ይህንን በጎ ተግባሩን በማስፋትና በማሳደግ በ2006 ዓ.ም በድሬዳዋ አስተዳደር በተሰጠው ከሊዝ ነፃ 5000 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ባለ አንድ ወለል ህንፃን ሰርቶ በማጠናቀቅ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ አመራሮች ፣ የሀይማኖት አባቶችና ፣ አርቲስቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ቋሚ ተጠሪ እና የብልፅግና ፓርቲ የድሬደዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ አስተዳደሩ ከምንግዜውም በላይ ሰዉ ተኮር በጎ ተግባራትን መሰረት ያደረገ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዉ ትናንት ሀገራችንን ሲያገለግሉ የነበሩ አረጋዉያን ዛሬ በተራችን እኛ ልናገለግላቸዉ ማዕከሉ ተግንብቶልናል ብለዋል ።በቀጣይም አስተዳደሩ ማዕከሉን በመደገፍ ከጎኑ ነን ብለዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሁክሚያ መሐመድ በበኩላቸው አረጋዊያን የሀገር ባለዉለታዎች መሆናቸዉን ጠቅሰው ማህከሉ ከሁለት መቶ በላይ አረጋዉያንን ተቀብሎ ለመርዳት በመዘጋጀቱ በቀጣይ ለሚኖሩ ድጋፎች ሁሉም አካል የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ።

የዳዊት ለአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዱኛ ሀይሌ በማህበሩ ስም ለተደረገላቸው ምስጋና አቅርበዋል በቀጣይ ድጋፋቹ አይለየን ብለዋል ።

ህንፃዉ 23 መኖሪያ ቤት እና 12 መፀዳጃና ሻዉር ቤቶች ሲኖሩት 300 ያህል ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽም አካቶ ይዟል ። ይህም 260 ያህል አረጋዉያንን የማስተናገድ አቅም አለዉ ።

በምረቃ ስነስርአቱ ላይ በአርቲስቶች በተለያየ የገቢ ማሰባሰቢያ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ከአራት መቶ ሺ ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *