የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ሀይል ባካሄደው የጋራ ስምሪት እና በወሰደው ጠንካራ እርምጃ የሽብርተኛው የሸኔ ቡድን አባላትን በመደምሰስ እና በመማረክ ቡድኑ ይንቀሳቀስባቸው የነበሩ አካባቢዎችን ነፃ በማውጣት ወደ አስተማማኝ ሰላም መመለስ መቻሉ ተገለፀ።

በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ፤ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የጸጥታ ሀይልን በመወከል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ሀይል ባካሄደው የጋራ ስምሪት እና በወሰደው ጠንካራ እርምጃ 43 የጠላት ሀይል መደምሰሳቸውን የገለፁ ሲሆን “ጃል ሐረርጌ” የተሰኘው የቡድኑ መሪ ከተደመሰሱት መሀከል መኖሩን እና ጃል ቦባሳ የተሰኘ የቡድኑ ምክትል መሪ ደግሞ በውጊያ ሰዓት ተመቶ በመቁሰል እንደተማረከና በተመሳሳይም ጃል ራሳ የተባለው የቡድኑ ምክትል በቁጥጥር ስል መዋሉን አመላክተዋል።

የሽብር ቡድኑ ይጠቀምባቸው የነበሩ 68 ክላሺንኮፍ ጠመንጃዎች፣ አንድ ጂኤም ስሪ፣ ስምንት ቦንቦች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጥይቶች እና የወገብ ትጥቆች መያዙንም ኮሚሽነር አለሙ የገለፁ ሲሆን፤ ከሽብር ቡድኑ ጋር የተለያየ ግንኙነት የነበራቸውን 34 ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል ዘጠኝ መዝገብ መከፈቱንና አራት ያህል መዝገቦችም ለአቃቢ ህግ መላካቸውን ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ በድሬዳዋ አስተዳደር እና በአጎራባች በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ሰርጎ በመግባት የተለያዩ የሽብር ስራዎችን በመስራት የሰው ህይወትን በማጥፋት እንዲሁም ብሄርን ከብሄር በማጋጨት ሁከት ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን ኮሚሽነር አለሙ ገልፀው፤ በምስራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ኃይል ማለትም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ምስራቅ ዕዝ፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል፣ በድሬዳዋ ፖሊስ የወንጀል መከላከል ሀይል፣ በኦሮሚያ ፖሊስ ፀረ ሽምቅ እና ልዩ ሀይል፣ በሶማሌ ልዩ ሀይል፣ በድሬዳዋ ሚሊሻ እና በኦሮሚያ ሚሊሻ በጋራ ትብብር ባከናወኑት የተቀናጀ ስራ የሽቡር ቡድኑን በመደምሰስ በድጋሚ እንዳይመለስ አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን አመላክተዋል።

ኮሚሽነር አለሙ ማህበረሰቡ ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመቆም የሽብር ቡድኑ በቁጥጥር ስል እንዲውል ለፀጥታ ሀይሉ የተለያዩ መረጃዎች ሲያቀብል መቆየቱን ገልፀው፤ በአጠቃላይ በተገኘው ድል የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸው አቅርበዋል።

በመጨረሻም ማህበረሰቡ በቀጣይም እንደ ሁልጊዜው ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመቆም ሰላሙን አስጠብቆ እንዲያስቀጥል ኮምሽነር አለሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *