የእግር ኳስ ውድድሮች ወረዳን ከወረዳ ብሎም ከተማን ከከተማና ሀገርን ከሀገር በማስተሳሰር ወዳጅነትን እንደሚያጠናክሩ ተገለፀ

የድሬዳዋ አስተዳደር የወረዳ ሁለት ወጣቶችና ስፖርት ማስተባበሪያ ከኢለፈንት ቢት ጋር በጋራ በመሆን የበጋ ወራት የ1ኛ ደረጃ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ውድድር ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

በዚህም በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማስፋፋትና ማልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ ዱሪ በስፖርት የዳበሩ ብቁ ወጣቶችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ፤ የእግር ኳስ ውድድሮች ወረዳን ከወረዳ ብሎም ከተማን ከከተማና ሀገርን ከሀገር የሚያስተሳስር፣ የእርስ በእርስ ወዳጅነትንም የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።

አቶ ኢብሳ አያይዘውም እንደነዚህ አይነት ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙ ሲሆን ለውድድሩ መሳካት የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እግር ኳስ የሰላም፣ የአብሮነትና የፍቅር መገለጫ በመሆኑ በውድድሩ የሚሳተፉ ቡድኖች በአጠቃላይ ጨዋታውን በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነትና ስነ-ምግባር እንዲያጠናቅቁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ የወረዳ 02 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ ናቸው።

አቶ አቤል አያይዘውም በውድድሩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ቡድኖች ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከት አመላክተዋል።

በውድድሩ በአጠቃላይ 8 ቡድኖች ይሳተፋሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *