በዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ Urban Resilience and Land (URL), Practice Manager በሆኑት Mr. Abhas K. Jha የተመራ ልዑካን ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር በዓለም ባንክ ድጋፍ የተሰሩ ስራዎች ላይና ስራዎቹን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ከአስተዳደሩ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ፤ በመስክ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በዚህም በውይይት መድረኩ የተገኙት የፋይንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ግርማ ተሰማ ባለፉት ዓመታት በዓለም ባንክ ድጋፍ በ UIIDP ፕሮግራም እንዲሁም በአስተዳደሩ ድጋፍ በድሬዳዋ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ፤ የኮብልስቶን ንጣፎች፣ የጎርፍ መከላከያ ግድቦች፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች እንዲሁም የመንገድ ላይ መብራቶች ተከላና ሌሎችም ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
አቶ ግርማ አያይዘውም በፕሮጀክቱ ለማህበረሰቡ የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ፣ የተቋማት ፕሮጀክትን የመምራት፣ የማቀድ እና የመተግበር አቅም መጎልበቱን እንዲሁም የአስተዳደሩን የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
በቀጣይ ፕሮግራሙ እንደ አስተዳደር እንዲቀጥል በዓለም ባንክ በኩል ፍላጎት መኖሩንና በተለይም በቀጣይ በምስራቅ ኢትዮጵያ ኮሪደር ላይ ድሬዳዋን ማዕከል አድርጎ በ UIIDP ፕሮግራም ምትክ አዲስ ፕሮግራም ለመቅረፅ የታቀደ መሆኑን አቶ ግርማ ገልፀው ለሚቀረፀው ፕሮግራም ግብአት የሚሆን ሰፊ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ Urban Resilience and Land (URL), Practice Manager የሆኑት Mr. Abhas K. Jha በበኩላቸው በአጠቃላይ በዓለም ባንክ ድጋፍ በድሬዳዋ የተከናወኑ ስራዎች ላይ ውይይት በማድረግ በተጨባጭ የተሰሩ ስራዎችን ወርደው መመልከታቸውን የገለፁ ሲሆን፤ በመስክ ምልከታቸውም በድሬዳዋ አስተዳደር በዓለም ባንክ ድጋፍ የተተገበሩ ፕሮጀክቶች የነዋሪውን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ልዑኩ በድሬዳዋ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችንም ጎብኝቷል።


