የመንግስት ቤቶችን ምቹ በሆነ ሁኔታ ለማስተዳደር በተሻሻለው የአሰራር ስርአት መሰረት የቀበሌ ቤቶችን የአስተዳደር ሂደት ዲጂታላይዝ በሆነ መልኩ ለመምራትና ድሬዳዋ የምትገኝበትን የልማት ግስጋሴ በሚመጥን መልኩ የቀበሌ ቤቶችን ለመገንባት እና ለማዘመን ቤቶቹን በአንድ ማዕከል መሰብሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ርክክብ መደረጉ ተመላክቷል።
በዚህም በርክክብ መርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የመንግስት ህንፃዎችና ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ ሙሳ ቤቶቹን ተረክቦ ለማስተዳደር በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ አሰራሩ ዲጂታላይዝ መሆኑ ለነዋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
አቶ ኢብሳ አያይዘውም በተለይም ቤቶቹን ተረኛ ለሆኑ ነዋሪዎች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለማስተላለፊ በሲስተም የታገዘ አሰራር እንደሚተገበር ያመላከቱ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ሲተገበር የቆየው የክፍያ አሰራር የነዋሪዎችን ጊዜ የሚፈጅና ቀልጣፋ አለመሆኑን አንስተው አሁን ላይ ግን የክፍያ ሲስተሞች ከቴሌ ጋር በመተሳሰራችው በቀላሉ በእጅ ስልክ ክፍያን መክፈል እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በመጨረሻም አቶ ኢብሳ ወረዳው ስራዎችን በቁርጠኝነት በመስራቱ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ወረዳዎችም ይህንን ስራ በአርዓያነት ሊወስዱት ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የወረዳ 02 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤል ምስራቅ በበኩላቸው ወረዳው ለ 5 ወራት የቀበሌ ቤቶችን የማጥራት ስራ መሰራቱንና በዚህም 100 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀበሌ ቤት ሕጋዊነት መምጣታቸውን ተናግረው በአጠቃላይ ወረዳው በዛሬው ዕለት 410 ቤቶችን ያስረከበ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ አቤል አያይዘውም 420 የቀበሌ ቤት ተረኞችም ለድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ መተላለፋቸውን ያመላከቱ ሲሆን፤ አሰራሩ ዘመናዊ እና በማዕከል መሆኑ የማህበረሰቡን የቤት ጥያቄ በተቀላጠፈ መልኩ ለመፍታት ፣ የቀበሌ ቤቶችን በትክክል ለሚገባቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም መንግስት ከቤቶቹ ማግኘት የሚገባውን ገቢ በአግባቡ እንዲያገኝ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
የቀበሌ ቤቶችን የማጥራት ስራ ሂደት ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሰራ እንደነበረ የጠቀሱት ደግሞ የወረዳው ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ምንተስኖት ትግስቱ ሲሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች ላደረጉት ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


