የፋሲል ግቢ ተውቦ እና አምሮ ለዳግም ውልደት መብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋሲል ግንብ የትም የማናገኘው ውድ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፣ “በእጃችን ስላለ ግን የሚገባውን ዋጋ አልሰጠነውም” ብለዋል።
“ይህን አባቶቻችን ያስረከቡንን ወርቅ ሀብት ይዘን ሀገር ብናለማ ኢትዮጵያ ዛሬ ተረጂ እና ለማኝ አትሆንም ነበር” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
“ዋናው ችግራችን እኛ እናንስና ታላላቆቹን ጎትተን መተካከል መፈለጋችን ነው”፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከእነዚያ ታላላቅ መሪዎች በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው አንሰው ትላልቁን ጎትተው የሚያሳንሱ በመበራከታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
ታላቆችን ማድነቅ እና ማክበር፣ የታላላቆችን ሥራ መመርመር ሲጀመር በእነሱ ሥራ ላይ ጡብ በመጨመር የተደመረ ዕድገት ሊያመጣ እንደሚችል ነው የተናገሩት።
ታላላቆችን ማሳነስ እና ሥራቸውን ማኮሰስ ግን የሚያቀጭጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ “ትላንትናችን መታወቂያችን እና መታወሻችን በመሆኑ ትላንትናችንን መርሳት የለብንም” ብለዋል።
ኋላውን ማስታወስ የሰው ተፈጥሮ መሆኑን እና ኋላውን ማስታወስ የቻለ ደግሞ ወደ ፊት ለመራመድ አቅም እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።
ጎንደር በትላንቷ ታሪክ ላይ ውበት መጨመሯን ጠቅሰው፣ ታዳጊዎች የነገ ብሩህ ተስፋቸው እዚህ ውስጥ ስለሚገኝ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።


