በድሬዳዋ ከሚስተዋለው የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞ የፕላስቲክ አጠቃቀምና ፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ስርዓትን ለመቀየር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተጠቆመ

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን “ፅዱ ኢትዮጵያን እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በአስተዳደር ደረጃ ለሁለተኛ ዙር በመከናወን ላይ የሚገኘው የንቅናቄ ስራዎች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ መሐመድ አባመጋል በስድስት ወራት ንቅናቄው በፕላስቲክ አወጋገድ ፣ በውሃ እና አፈር ብክለት ፣ የአየር ብክለትን በመከላከል ፣ የድምፅ ብክለትን በመቆጣጠር እንዲሁም እየተጠናቀቀ በሚገኘው የጥቅምት ወር በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ላይ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ስራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ አስታውሰዋል።

አቶ አብዱ በመግለጫቸው አክለውም የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ስርዓትን በሚፈለገው መጠን እየተከናወነ አለመሆኑን ያነሱ ሲሆን ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ እና ለሌላ አገልግሎት መልሶ መጠቀም የድሬዳዋ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ (Sanitary Landfill Area) ቶሎ እንዳይሞላ ከማገዙም ባለፈ ስፍራው አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ለማስተካከል ያግዛል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀምሌ ወር 2017 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ በሀገር ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች የፌስታል ምርት ማምረትም ሆነ ከውጪ ምርቱን ማስገባት የሚከለክል ህግ የተደነገገ መሆኑን ገልፀው እስከ ታህሳስ 2018 ዓ.ም ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ በመጪዎቹ ወራት ህጉ ወደ ትግበራ እንደሚገባም አረጋግጠዋል።

አንድ ሚሊየን እየተጠጋ የሚገኘው የድሬዳዋ ነዋሪን የፅዳት እና ውበት ኤጀንሲ በሚያከናውናቸው ስራዎች ብቻ የቆሻሻ አወጋገድና የአካባቢ ብክለትን መከላከል እንደማይቻል አፅዕኖት ሰጥተው የገለፁት አቶ አብዱ በቀጣዩ ወር የዘመቻው ስራው ተጠናቀቀ ማለት የአካባቢ ጥበቃ ስራው አለማብቃቱን በመረዳት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።

ስራ አስኪያጁ በሌላ በኩል በከተማዋ እየተባባሰ የመጣውን የወባና ሌሎች በትንኝ ንክሻ የሚተላለፉ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር በተለይም በቡቲጂ ወንዝ ላይ የሚስተዋለውን የደረቅ ቆሻሻ በማስወገድ ምክንያት በወንዙ ውሃ በመከማቸቱ ለትንኝ መራቢነት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ስለሚገኝ ህብረተሰቡ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ የመያዝና የማስወገድ ተግባራት ማከናወን እንደሚገባና እራሱ ከበሽታ መከላከልና የአካባቢውን ንጽህና መጠበቅ እንደሚገባው ገልጸዋል እንደሚገባው ለስድስት ወራት የሚቆየውና “ፅዱ ኢትዮጵያን እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ እንዲሁም በአስተዳደር ደረጃ ለሁለተኛ ዙር እየተከናወነ የሚገኘው የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ ግንቦት 28/2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ ሰኔ14/2017 ዓ.ም ደግሞ በድሬዳዋ መጀመሩ ይታወሳል።

መረጃውን ያደረሰን፦የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *