ግባችን ሥራ መፍጠር፣ ዕድልን ማስፋት እና የሕዝባችንን አቅም የሚያንፀባርቅ ኢኮኖሚ መገንባት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባ ዘመናዊ የበቆሎ ማቀነባበሪያ እና የምግብ ማምረቻ ሥራ አስጀምረዋል።

ብራውን ፉድስ የተሰኘው ዘመናዊ የበቆሎ ማቀነባበሪያ እና የምግብ ማምረቻ ከበቆሎ፤ ቦሎ፣ ሽምብራ እና ሌሎች እህሎች ቅይጥ ምግቦችን አዘጋጅቶ ለምግብ፣ ለመጠጥ እና ለእንሰሳት መኖ ኢንዱስትሪዎች የሚያቀርብ ነው።

በሥራ ማስጀመሪያው ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፥ ግባችን ሥራ መፍጠር፣ ዕድልን ማስፋት እና የሕዝባችንን አቅም የሚያንፀባርቅ ኢኮኖሚ መገንባት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በደብረ ብርሃን ያየነው ጅማሮ ከፋብሪካ ማቆም በላይ ለክልላችን ምርታማነት እና በራስ መተማመን የአዲስ ዘመን ማሳያ መሠረት ነውም ብለዋል።

አማራ ክልል ከፍተኛ አቅም እና ለም አፈር አለው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን አቅም በአርሶ አደሮች፣ በሠራተኞች፣ በሥራ ፈጣሪዎች እና በአመራሩ የተባበረ ክንድ ወደ እሴት መለወጥ ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል።

መንግሥት እነዚህን ስጦታዎች ወደ እውነተኛ ልማት ለመቀየር ያለማቋረጥ እንደሚሠራ በመግለጽም፤ የሚያገናኙን መንገዶችን፣ ብርሃን የሚሰጡ የኃይል መስመሮችን እና ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን በመዘርጋት በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የምንሻው በፍጥነት እና በጥራት ሠርቶ ማጠናቀቅ የሚችል አመራር፣ ግልጽነት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እና ለመጭው ትውልድ የሚያስብ መንግሥት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዛሬ ባገኘነው ድል አንኩራራ፣ እረፍትም አናብዛ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ ብልጽግና የሚደረገው ሩጫ ገና መጀመሩን በአግባቡ በመረዳት መፍጠሩን፣ ጀምሮ መገንባቱን፣ ጨርሶ ማስመረቁን መቀጠል አለብን ብለዋል።

የምግብ ማቀነባበሪያው በቀን 300 ሜትሪክ ቶን የማምረት ዓቅም ሲኖረው፤ 60 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚይዝ ማከማቻም ተዘጋጅቶለታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *