የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አንባሳደር አሌክስ ላሜክ ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች ስራዎችን በጋራ አጠናክሮ ለመስራት በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል።
በዚህም በመድረኩ ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤ ድሬዳዋ ቀንም ለሊትም እንቅስቃሴ ያላት ሰላማዊ ከተማ መሆኗን በመግለፅ ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ያላት ምቹ ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ሰተዋል።
ድሬዳዋና ፈረንሳይ ከ126 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ያመላከቱት ከንቲባ ከድር ፈረንሳይ በድሬዳዋ በባቡር ስራዎች እንዲሁም በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ትምህርት ቤትና በሌሎችም ዘርፎች አሻራዋን ማኖሯን አመላክተዋል።
ከሶስት የፈረንሳይ ከተሞች ጋር ድሬዳዋ እህትማማች ከተማ በመሆን በትምህርት፣ በባህል፣ በስፖርት እና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሰራች እንደምትገኝ ክቡር ከንቲባ ከድር ጠቁመው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አንባሳደር አሌክስ ላሜክ በበኩላቸው ፈረንሳይ እና ድሬዳዋ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች ስራዎችን በጋራ የመስራቱን ሂደት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።


