የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ::

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤትና ተጠሪ ተቋማት አመራር እና ሰራተኞች ዛሬ ከሰዓት በኋላ የኤች አይ ቪ ኤድስ እና የነጭ ሪቫን ቀንን አከበሩ።

“ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን ማረጋገጥ ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ 37ኛ ጊዜ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ38ኛ ጊዜ የሚከበረው አለም ዓቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን እና “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የነጭ ሪቫን (የጸረ ጾታዊ ጥቃት) ቀንን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤትና ተጠሪ ተቋማት አመራር እና ሰራተኞች በዛሬው ዕለት አክብረዋል።

በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደር እና የቅሬታ አፈታት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰዓዳ አዋሌ የአለም የኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር የኤች አይ ቪ ኤድስን ስርጭት ለመግታት ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታትና ጤናማ፣ አምራች እና ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት አመራሩና ህብረተሰቡ ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት ወ/ሮ ሰዓዳ ያሳሰቡ ሲሆን፤ ዕለቱ ሲከበር በቫይረሱ ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

ወ/ሮ ሰዓዳ አያይዘውም ለሥርዓተ ጾታ እኩልነት የወንዶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንዳይፈጸም ወንዶች በትብብር ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

‎የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በማንኛውም ሁኔታ ጾታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃትን እንዲሁም ትንኮሳን ለመከላከል የሚደረግ ንቅናቄ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ፌኑስ አብዱልጀባር ናቸው።

በመድረኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት እንዲሁም የጥያቄና መልስ ውድድር ተከናውኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *