ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ተደራሽነቱን በማስፋት በማያ ሲቲ በሃረማያ ከተማ አዲስ ቅርንጫፉን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ የፋይናንስ ተደራሽነቱንና አካታችነቱን በማጠናከር የተቋሙ ታላሚ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም መጠነኛ ገቢ ያላቸውና አነስተኛ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች የተሰማሩትን ብሎም ወጣቶችና ሴቶችን በስፋት በሚሰጣቸው የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶቹ እየደረሰ ይገኛል።
ዛሬም የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት አዲስ ቅርንጫፉን በታሪካዊው የሃረማያ ሃይቅ መገኛ ሃረማያ ከተማ በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የድሬ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ተሾመ አበበ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በድሬዳዋ፣በሐረርና በጅግጅጋ በከፈታቸው ቅርንጫፎቹ በመደበኛ፣በወለድ አልባ፣በሊዝ ፋይናንሲንግና በዲጂታል የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶቹ ሰፊውን ማኅበረሰብ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ደግሞ ተቋማቸው ተደራሽነቱን በማስፋት በሃረማያ የአካቢውን ህዝብ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት ቅርንጫፍ መክፈቱን ተናግረዋል።
ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በተለይም ወጣቶችና ሴቶችን ማዕከል በማድረግ የሚሰራ ተቋም በመሆኑ የሊዝ ፋይናንሲንግን ጨምሮ ባሉት አገልግሎቶቹ በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ የድርሻውን ሚና በመወጣት ለአካባቢው ለወጣቶችና ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመሥራትና የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማንቀሳቀስ የቅርንጫፉን ተደራሽነት የማስፋት ሥራዎች በሰፊው ይሰራሉ ብለዋል።
በምረቃት መርሃግብሩ ላይ የተገኙት ተጋባዥ ዕንግዶች ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ በሃረማያ ቅርንጫፍ መክፈቱ እንዳስደሰታቸው በመግለፅ የቅርንጫፉ መከፈት የአካባቢውን ኅብረተሰብ በባንክ ደረጃ የማያገኛቸውን አገልግሎቶች እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
በምረቃት መርሃግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በቅርንጫፉ ይፋዊ ምርቃት መርሃግብር ላይ የተገኙ ዕንግዶችም ስለ ድሬ ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶች ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን የሃረማያ ቅርንጫፍ ጉብኝትም ተካሂዷል።


