በድሬዳዋ አስተዳደር ከ 2 ሺ 4 መቶ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክትን ወደ ስራ ለማስገባት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተደረገ::

ኤስ ኦ ኤስ (SOS) የህፃናት መንደር በድሬዳዋ አስተዳደር ለ አምስት ዓመታት የሚተገበር ”Green growth -empowering youth for green future project ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ዕለት ፕሮጀክቱን ወደ ስራ ለማስገባት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ ኃላፊ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ፕሮጀክቱ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰራ እና ከ2,400 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

ወ/ሮ ፈጡም አያይዘውም ፕሮጀክቱ ለአምስት አመታት እንደሚቆይ እና ለወጣቶች ክህሎት መር የስራ እድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር የሀረር ፕሮግራም የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ቢሮ አስተባባሪ አቶ ሚካኤል ስንታየሁ ፕሮጀክቱ ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ለማሰልጠን ከታቀደው ውስጥ 60% የሚሆኑት ሴቶች 5%ቱ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ወገኖች መሆናቸውን አቶ ሚካኤል ያመላከቱ ሲሆን፤ፕሮጀክቱን ስኬታማ ለማድረግ ከግል የፋብሪካ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

የኢትዮ ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ በበኩላቸው ድሬዳዋ የኢንደስትሪ ከተማ መሆኗን ጠቅሰው በፕሮጀክቱ ወጣቶችን በማሰልጠን ለኢንደስትሪው የማቅረብ ስራ በስፋት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

አቶ ታደለ አያይዘውም ፕሮጀክቱ ለድሬዳዋ ወጣቶች የስራ እድልን በመፍጠር አሁን ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስና የስራ ባህልን በማጎልበት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *