ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፓን አፍሪካ እሳቤ አዲስ አብነት ነው፡- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ከኃይል ማመንጫ ግድብነት ባሻገር በራስ አቅም የራስን መሻት ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ የፓን አፍሪካ እሳቤ አዲስ አብነት መሆኑን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ተናገሩ።

የሩስያው አርቲ ሚዲያ ባዘጋጀው የአፍሪካ ሚዲያ እውቅና መድረክ የሚታደሙ የሀገራት የኮሙኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴሮች እና ተወካዮች፣ የቀድሞ የፓን አፍሪካ መሪዎች ልጆች፣ የአፍሪካ ሀገራት የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አዲስ አበባ ገብተዋል።

ትናንት ምሽት በነበረው የእንግዶች የመክፈቻ ንግግር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ “የበለጸገች፣ የተባበረች እና የተረጋጋች አፍሪካን ያልሙ የነበሩ ቀደምቶቻችንን መሻት ለማሳካት ልጆቻቸው እና የሚዲያ ተቋማት ኢትዮጵያ ላይ በመገኘታችሁ ደስ ብሎናል፤ ኮርተናልም” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፥ “አሁንም በቀደምቶቻችን የአንድነት እና የትብብር መንፈስ የአህጉራችንን ጸጋ እናለማለን፤ የበለጸገች አፍሪካን እውን እናደርጋለን፤ የተዛቡ ትርክቶችንም እንገራለን” ብለዋል።

አቶ ተስፋሁን በመልዕክታቸው፥ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ማዕከልነቷን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በራስ አቅም በማሳካት እንደገና ማስቀጠሏን አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያውያን ላብ፣ ደም፣ ገንዘብ እና ዕውቀት አዋጥተው በሉዓላዊ ግዛታቸው ውስጥ የራሳቸውን ውኃ ለመጠቀም ሕዳሴ ግድብን እውን ያደረጉት በቀደምቶቹ ፓን አፍሪካዊ እሳቤ ላይ ተመርተው ነው” ብለዋል።

ይህ ደግሞ ለላቀ ፓን አፍሪካዊ ድል የሚያነሣሣ ሌላ አዲስ መሠረት መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

ሕዳሴ ግድብ የነበሩ ትርክቶችን የለወጠ፣ የዓለምን ትኩረት የሳበ እና የኢትዮጵያን የመቻል አቅም ያሳየ ፕሮጀክት እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “ሕዳሴ የግጭት ሳይሆን የአንድነት እና የትብብር ማዕከል፣ የውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊነት ማሳያ ነው” ብለዋል።

ከሕዳሴ ግድብ ባሻገር ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ፣ በከተሞች ልማት፣ በኤአይ እና በሌሎችም መስኮች ከፍተኛ እመርታ እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው፤ ከ40 በላይ ሚዲያዎች ይህን በአካል ለመታዘብ መምጣታቸው ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አክለዋል።

ለዚህም ውድድሩን በማዘጋጀት ከፍተኛ ሚና ለተወጣው አርቲ ሚዲያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምሽቱ መርሐ ግብር የኔልሰን ማንዴላ፣ ኩዋሜ ንክሩማህ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ጁሊዬስ ኔሬሬ፣ ኬኔት ካውንዳ እና ሌሎችም የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ የቀድሞ መሪዎች ልጆች፣ የሚዲያ ኃላፊዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተገኝተዋል።

የአፍሪካ ሚዲያ ዕውቅና መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ይካሄዳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *