ለፋይዳ መታወቂያ ደህንነት የሚውል የዲጂታል ሰርተፊኬት አገልግሎት በይፋ ተጀመረ::

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ደህንነት አገልግሎት የሚውል የሩት ሰርተፊኬት ባለስልጣን አገልግሎት በይፋ አስጀመረ፡፡

አስተዳደሩ ከጥቂት ወራት በፊት ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ደህንነት አገልግሎት የሚሰጥ ዲጂታል ሰርተፊኬት ለማምረት የሚውለውን የሩት ሰርተፊኬት ባለስልጣን አገልግሎት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም በተመሳሳይ ሁኔታ ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ደህንነት የሚውለውን አገልግሎት አስጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን በማገባደድ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ጀምራለች፡፡

ይህም የሕዝብ አገልግሎቶች፣ የፋይናንስ ተሳትፎ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በታመኑ ዲጂታል ሥርዓቶች የሚከናወኑበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀገራችንን ዲጂታል ምህዳር ተአማኒነት ለማጠናከር እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚደግፉ ዲጂታል አገልግሎቶችን አስተማማኝ መሠረት ለመገንባት ወሳኝ የሆነ ምዕራፍ ነው ሲሉ መግለጻቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ ለፋይዳ መታወቂያ ደህንነት የሚውል የዲጂታል ሰርተፊኬት አገልግሎት መጀመሩ ኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ እምነት የሚጣልበት እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

በዚህም አገልግሎት በፋይዳ ፕሮግራም ሥር ለዜጎች የሚሰጠው እያንዳንዱ ዲጂታል መታወቂያ ትክክለኛ፣ ሊረጋገጥ የሚችል፤ እና ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን የሚያስችል ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *