ኢትዮጵያ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ እና ብሔራዊ ሉዓላዊነትን መጠበቅ ትቀጥላለች ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ብሔራዊ ስትራቴጂን በተመለከተ በሰፈረ መቅድም፣ ፕሮጀክቱ ከዲጂታል ዘመን አደጋዎችና ተግዳሮቶች ባሻገር፣ ልማትና ሉዓላዊነትን በማጎልበት የኢትዮጵያን የልማት ጎዳና በራሱ ለመቅረጽ ቁርጠኛ መሆኗን ቀጥላለች ብሏል አገልግሎቱ።
“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂ፣ በዓላማ፣ በቁርጠኝነትና በችሎታ ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ ምላሽ መስጠት መሆኑንም አገልግሎቱ ባሰፈለው ፅሑፍ ገልጿል፡፡
ስትራቴጂው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2030 ታላቅ ልማትን ለማስመዝገብ ያለውን ከፍተኛ ምኞት የሚያሳይ ሲሆን፣ በኢኮኖሚ፣ በመንግሥታዊ አስተዳደርና በማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን የምትመራባቸውን መርሆዎች የዲጂታል ለውጡ በኢትዮጵያ ማንነትና እሴቶች የተደገፈ ሲሆን፣ ለሁሉም ዜጎች አካታች፣ ፍትሃዊ እና ትርጉም ያለው እንዲሆን ተደርጎ ስለመዘጋጀቱም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ እየተገነቡ ባሉ እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት፣ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅና ብሔራዊ ሉዓላዊነትን መጠበቅ ትቀጥላለች ያለው አገልግሎቱ፤ በተጨማሪም፣ በዲጂታል ሥርዓት ውስጥ ማንም ወደ ኋላ እንደማይቀር ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጿል።
ይህ ቁርጠኝነት በዋናነት በሰው ላይ መስራት እና ፈሰሰስ ማድረግ እንደሚጠይቅ በመግለጽ፤ ይህም ከተሞችንና ገጠራማ አካባቢዎችን ከፍ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ዲጂታል አስተሳሰብንና የፈጠራ ባህልን በማጎልበት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ዘመን የሁሉን አቀፍ ዕድገትና ብልጽግና እንዲመራት ለማድረግ መዘጋጀቱን ያመለክታል ብሏል።
“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” በዓለም አቀፍ አጋሮችና በዜጎች ትብብር፣ የጋራ ዕድገት መንፈስን በማንፀባረቅ የሚተገበር ነው መሆኑም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ የራሷን የዲጂታል ልማት ጎዳና ስትቀይስ፣ “ጥንካሬ ያላት፣ ሉዓላዊ እና ለወደፊት ዕድሎች ዝግጁ የሆነች ዲጂታል ኢትዮጵያ” ለመገንባት መተባበርን ይጠበቅብናል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስገንዝቧል፡፡


