“በኮሪደር ልማት ስራ አቧራን አራግፎ ከተማን ማስዋብ በመንግስት በጀት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በማህበረሰቡ ተሳትፎ መሆን እንዳለበት የጅማ ከተማ ተሞክሮ ማሳያ ነው” – ከንቲባ ከድር ጁሀር

በከንቲባ ከድር ጁሃር የተመራው እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የዘጠኙም ከተማ ወረዳዎችንና የገጠር ክላስተር አመራሮችን የያዘው የድሬዳዋ አስተዳደር የልዑካን ቡድን በጅማ ከተማ ጉብኝት አከናወነ።

በጉብኝታቸውም የከተማዋን የወንዝ ዳር ተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ፣ አምራች ኢንደስትሪዎችን ፣ ታሪካዊውን የአባ ጅፋር ቤተመንግስትን ጨምሮ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ቃኝተዋል።

በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፎች እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ፥ የእንጨት ስራ ውጤቶች ፋብሪካን ፣ የፕላስቲክ ውሀ ማጠራቀሚያዎች ማምረቻን ጨምሮ የተለያዩ አምራች ድርጅቶችንም ተመልክተዋል።

ልዑኩ በማስከተል በቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ረገድ የማሻሻያ እድሳት የተደረገለትን ታሪካዊው የጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግስትን የተመለከተ ሲሆን በውስጡ ያሉትን ጥንታዊ መገልገያዎችንና ክፍሎችን ቃኝተዋል።

በከተማዋ እየተሰራ የሚገኘውን የወንዝ ዳር ተፋሰስ ልማትን እንዲሁም በኮሪደር ልማት አፍርሶ ግንባታ ተጠናቀው ስራ የጀመሩ ጎዳናዎችንና የአገልግሎት ሰጪ የንግድ ቦታዎችንም ተመልክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት በኮሪደር ልማት ስራ አቧራን አራግፎ ከተማን ማስዋብ በመንግስት በጀት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በማህበረሰቡ ተሳትፎ መሆን እንዳለበት የጅማ ከተማ ተሞክሮ ማሳያ ነው ብለዋል።

በጅማ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ ከ14 ሺህ ዘጠኝ መቶ በላይ ቤቶችን አፍርሶ መስራቱ የአመራሩ ቁርጠኝነት የት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቋሚ ነው ብለዋል።

ታሪካዊው የጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግስትን የቀደመ መልኩን እንዲጠብቅ ተደርጎ በተሰራው ማሻሻያ ፤ ከዚህ ቀደም በዙሪያው የነበሩ ህገ ወጥ የግለሰቦች የቤት ግንባታና ወረራን በማስቆም ያማረ ግቢን በማቆየት ለትውልድ ተሻጋሪ ቅርስ እንዲኖር ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

ድሬዳዋ እና ጅማ የእህትማማች ከተማነት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች እንደሚክናወኑም ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *