የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የቁሉቢ ገብርዔል የንግስ በዓልን ለማክበር ወደ ድሬዳዋ ከተማ ለመጡ እንግዶች ደማቅ አቀባበል አደረጉ።

ታህሳስ 19/ 2018 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓልን ለመታደም ወደ ድሬዳዋ ለመጡ እንግዶች ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ እንዲሁም በአስተዳደሩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በድሬዳዋ መግቢያ የገነት መናፈሻ ኬላ ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በጋራ ባዘጋጁት በዚህ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መርሃ-ግብር ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለመጡት እንግዶች “የእንኳን ደህና መጣችሁ” እንዲሁም “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከንቲባ ከድር አያይዘውም ድሬዳዋ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) “ትንሿ ኢትዮጵያ” ተብላ በተሰየመችው መሰረት ስሟን በተግባር ያስመሰከረች የፍቅር፣ የሰላምና የአብሮነት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

በየወረዳውና በቤተክርስቲያን አካባቢዎች ላይ በማህበረሰቡ የተተከሉ ድንኳኖች እንግዶችን እያስተናገዱ መሆኑንም ከንቲባ ከድር ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮምሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው እንግዶቹ በድሬዳዋ በሚኖራቸው ቆይታ ሁሉ ፍጹም ሰላማዊ ጊዜን ማሳለፍ እንደሚችሉ ገልፀው፤ የድሬዳዋን የአብሮነት ተሞክሮ ለሌሎች አካባቢዎች በተሞክሮነት ሊወሰድ እንደሚገባ አመላክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *