አመታዊውን የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ በርካታ ምእመናን በተገኙበት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሯል።
የወረዳ 2 አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አቶ አቤል ምስራቅ በቀጠናው ካሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ጋር በመቀናጀት እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታይ ከሆኑ እህት ወንድሞች ጋር በጋራ በመሆን ለበዓሉ ታዳሚዎች ማእድ ማጋራት እንደተከናወነ ጠቁመዋል።
አቶ አቤል አያይዘውም ድሬዳዋ የአብሮነትና የፍቅር ከተማ መሆኗን ገልፀው፤ በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ እንግዶችም በሳቢያን ማደያ አካባቢ ሶስት ድንኳኖች ተጥለው እንግዶች እየተስተናገዱ መሆኑን አመላክተዋል።
በበዓሉ ላይ ሲያስተባብሩ ያነጋገርናቸው የእስልምና ተከታይ እህት ወንድሞች በድሬዳዋ ሁሉም በዓሎች በጋራ እንደሚከበሩ ያመላከቱ ሲሆን የዛሬው ማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብርም ለክርስትና እምነት ተከታይ እህት ወንድሞች ያለንን ፍቅር ለመግለፅ ያዘጋጀነው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ የለሊት ታክሲ ማህበር ለበዓሉ ታዳሚዎች የነፃ አገልግሎት ሰቷል።


