የግብርና ብድር አገልግሎት የገጠሩ ኢኮኖሚ ዘላቂ እድገት እንዲኖረው እንደሚያግዝ ተገለፀ::

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ የግብርና ብድር ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከድሬዳዋ ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር ተፈራርሟል።

በስነ-ስረአቱ ላይ የድሬደዋ ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንደ አገር የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማላቅ የተሻለ ለማድረግ የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑ ገልፀዋል።

እንደ ግብርና ቢሮ የአስተዳደሩ አርሶ አርብቶ አደር ተጠቃሚነትና እድገት የሚያግዙ ጉዳዮች እንዲጠናከሩ እንደ ቢሮ በርካታ ጥረቶች እንደሚደረጉ ባንኩ ያቀረበው የብድር አገልግሎት ይህንን ጥረት ሊያግዝ እንደሚችል ጨምረው ገልፀዋል።

ባንኩ ወደ ገጠሩ ማህበሩሰቡ ቀርቦ ለመስራት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው ከአስተዳደሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተቃኘ መልኩ በማሻሻል አገልግሎቱን ማስጀመር ይገባል ሲሉ ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በየደረጃው በዘርፉ ያሉ አካላት ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ ኑረዲን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድሬደዋ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ በቃና ባንኩ በብድር አገልግሎት ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዚህም ባንኩ ግለሰቦች አሊያም በቡድን ለተደራጁ አርሶ አደሮች ሁሉንም የገጠር ማህበረሰብ ያካተተ የብድር አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልፀዋል ።

ባንኩ ግብርናውን ለማዘመን በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው አዲሱ ብድር በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ያሉ አርሶ አርብቶ አደሮችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎች ከወለድ ነፃ ብድርን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ዳይሬክተሩ ከባንኩ የበላይ አመራር ጋር እንደሚያዩ ገልጸዋል።

የብድር አቅርቦቱ በዋናነት የስራ ማስኬጃ እንዲሁም የፕሮጀክት ፋይናንስ ብድር በሚል የተከፋፈለ ሲሆን:-

የስራማስኬጃ ብድር :-ለሰብል ምርት፣ እንስሳ እርባታና የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ብድር ናቸው።

የፕሮጀክት ፋይናናስ:-አትክልትና ፍራፍሬ ፣የወተትና የወተት ተዋፅኦ

የግብርና ማሽነሪ ብድር ናቸው።

አገልግሎቱ ከአጭር እስከ መካከለኛ ጊዜ የሚቆይ ብድር የቀረበ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

በአጠቃላይ በዚህ የብርና ብድር አገልግሎት እንደ አስተዳደር በርካታ አርሶ አርብቶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *