” የተቀናጀ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ለግብርና ሽግግር ስኬት ” በሚል መሪ ሀሳብ የ 2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር በዛሬው እለት በአሰሊሶ ክላስተር ገንደሪጌ ገጠር ቀበሌ ተካሂዷል ።
መርሀ -ግብሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ባለፍት አመታት በተሰሩ የአፈር እና ውሀ ጥበቃ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በአስተዳደራችን በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ለሚቀጥሉት 30 ቀናት በላቀ የህብረተሰብ ተሳትፎ የአፈር እና ውሀ ጥበቃ ስራዎቹ እንደሚከናወኑ ገልፀዋል።
ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር አክለውም ባለፍት አመታት ሲተገበር የነበረውን የተቀናጀ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ልምዶች በማስፋትና የተራቆቱ ተፋሰሶችን ወደ ነበሩበት በመመለስ የተፈጥሮ የመቋቋም አቅምን መገንባት ፣ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን መቀነስ እና የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉና እንደ ሀገር የጀመርነውን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግሩ እና ጠንካራ አቅምን የሚፈጥሩ ተግባራት ልዩ ትኩረት ተሰቷቸው እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል ።
በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በአጠቃላይ 37,927 የሰው ሀይል ከመሳተፍም በላይ በ 5,500 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የአፈር እና ውሀ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን በ 3 ነጥብ 7 በመቶ የመሬት መራቆትን መቀነስ የሚያስችል ስራዎች እንደሚሰሩም ነው የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሀ ማእድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ ያስታወቁት ።


