የተቀናጀ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ለግብርና ሽግግር ስኬት 2018ዓ.ም እንደ ዋሂል ክላስተር በሀርላ ቀበሌ በተካሄደ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ተጀምሯል።
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ የተፋሰስ ልማት የደን መራቆትን በመከላከል የደን ሽፋንን ለመጨመር፣የአፈርና ውሀ ጥበቃ ለማጎልበት፣የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይረዳል።የከብት መኖ አቅርቦትን ለመጨመር ያግዛል ብለዋል።
በዘንድሮው የተቀናጀ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት የመሬት መራቆትን በ3.7 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ እንደሚከናወን ፣ከአምሰት ሺህ አምስት መቶ በላይ ሄክታር የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ለማከናወን መታሰቡን፣ከ37 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በስራዉ ለማሳተፍ መታቀዱን ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ውሃ ማዕድና ኢነርጂ ቢሮን ወክለው በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት አቶ መሀመድ አሜ መንግስት የአርሶ አርብቶ አደሩን ዜጋ ህይወት የሚያሻሽሉ የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቲጂዎች በየግዜው ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
የተፋሰስ ልማት ከዚህ ቀደም በተበታተነ መንገድ ሲከናወኑ የነበሩ ስራዎችን በማቀናጀት በህዝብ ተሳትፎ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የገጠሩ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እንዲዳብሩ ከሚያግዙ አንዱ የተፋሰስ ልማት በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የዋሂል ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዲ ኑሬ በክላስተሩ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የተራቆቱ ተራሮችን እንዲያገግሙ ማድረግ መቻሉን አብረርተዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በህዝብ ለማከናወን የታቀዱ ስራዎችን በተቀመጠላቸው እቅድ መሰረት እንዲፈፀሙ እንደሚሰራም ገልፀዋል።


