በከተማዋ እየተመዘገበ ለሚገኛው ሁለንተናዊ ልማት እና ሰላም የአመራሩ እና የህዝቡ ለአንድ አላማ ተባብረው የመስራታቸው ውጤት እንደሆነ ተገለፀ።

ይህንን የአስተዳደሩን እድገት እና ሰላም ለማደፍረስ ህዝቡን እና አመራሩን ሆድ እና ጀርባ ለማድረግ የሚጥሩ አካላትን ማውገዝ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የኦሮሚኛ ቋንቋ የኪነጥበብ ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስት መሀመድ ቆጴ ተናግሯል።

የ1960 የኦሮሚኛ ቋንቋ የኪነጥበብ መነቃቃት ውስጥ ጉልህ አሻራ ከነበራቸው የዘርፉ አርቲስቶች መሀል የግጥም እና ዜማ ደራሲው መሀመድ አህመድ ሙሳ ወይም በቅፅል ስሙ መሐመድ ቆጴ ግንባር ቀደሙ ነው። የኦሮሚኛ ዘፈን እንቁ አሊ ቢራ “ሚላን ተኡ መሌ ገራን ቢያ ሂን በሁ” ከተባለው ስራው ጀምሮ፣ ለአብተው ከበደ ” ያድኒ ኮ ገመቴ ቲ “፣ ለሀሎ ደዌ ደግሞ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውን “በርባኔ ወልበራ” የሱ ቱሩፋቶች ናቸው።

የሀረር ሬዲዮ ጣቢያ የኦሮሚኛ ፕሮግራም ስርጭት መክፈቻ ላይ ባለው ንግግሩ ቆጴ የተባለ የእድሜ ልክ ቅፅል ስም አስገኝቶለታል። እሱም ” ሁሌም የድሬደዋ እና የሀረር ልጅ መሆኔ ያኮራኛል” በማለት ደጋግሞ ያናገራል።

በቅርቡ በከተማችን በተካሄደው የሼክ በክሪ ሳጰሎ የበጎ አድራጎት ድርጅት የምስጋና ስነስርዓት ላይ የተገኘው መሀመድ ቆጴ፥ በድሬደዋ እየተመዘገበ ባለው ልማት የህዝቡ እና የአመራሩ ቁርጠኝነት በተለይም የከተማዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የላቀ ስብእና ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው መረዳቱን ገልጿል።

ባለፉት 27 አመታት በከተማዋ የቀድሞ የህዝቡ አብሮ የመኖር ባህል የተሸረሸረበት እና አለመተማመን የነበረበትን አውድ የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ በማስተካክል በኩል ከንቲባው እና አመራሩ ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውን የጠቀሰው መሀመድ ቆጴ ይህን የተገኘውን ልማት እና ሰላም ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሀይሎችን ሴራ በማወቅ ይህን እኩይ ተግባር መታገል ይገባል ሲል ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *