“በፊት ላይ ቆሻሻ መጣያ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ በኮሪደር ልማቱ ገፅታቸው ተቀይሮ ውብና ሳቢ ማድረግ ተችሏል” – የወረዳ አራት ነዋሪዎች።

በድሬዳዋ በወረዳ አራት (04 ) እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ በፊት ላይ ቆሻሻ መጣያ የነበሩ አካባቢዎችን በመቀየር ውብና ሳቢ ማድረግ መቻሉን የወረዳው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በወረዳው እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የወረዳውን ገፅታ በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረ መሆኑን የገለፁት ነዋሪዎቹ ከኮሪደር ልማቱ በፊት ቆሻሻ መድፊያ፣ እንዲሁም የተለያዩ አልባሌ ተግባራት ይከናወኑበት የነበሩ ቦታዎች በአሁኑ ሰዓት በኮሪደር ልማቱ ፅዱና ማራኪ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

ነዋሪዎቹ አያይዘውም በወረዳው ከዚህ ቀደም አቧራ ያስቸግር እንደነበርና በምሽት ወቅት ለመንቀሳቀስ አደጋች እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በኮሪደር ልማቱ በተዘረጋው መብራት በነፃነት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ነዋሪዎቹ በቀጣይም ልማቱን ከመንግስት ጎን በመቆም ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የመንግስት የግዢና ንብረት ማሶገድ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው ደጋፊ አመራር የሆኑት አቶ ብሩክ ፈለቀ በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ ከፈታ፣ በመንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ አሸሽሎ የመስራት ስራ እንዲሁም ጋራ ላይ የሚገኙ ቤቶችን በቀለም የማሳመር ስራን ጨምሮ በርካታ የወረዳውን ገፅታ የሚያሳምሩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የስራና ክህሎት ቢሮ ም/ል ኃላፊና የወረዳው ደጋፊ አመራር የሆኑት ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በበኩላቸው ስራዎችን ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከኮሪደር ልማቱ በፊት ጠባብና ውብ ያልሆኑ የወረዳው አካባቢዎች ዘመናዊ መልክ በመያዝ ላይ እንደሚገኙ ጠቆሙት ደግሞ የወረዳው ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ያሲን ኢስማኢል ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *