በዚህም የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ የዲጂታል የኢትዮጲያን ጉዞ ለማፋጠን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) አሰራር ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ገልፀዋል።
በኤሌክትሮኒክስ ግዢን መፈፀም ብልሹ አሰራርን በመቀነስ ወጪና ጊዜን እንደሚቆጥብ የጠቆሙት ም/ከንቲባ ሀርቢ የአሰራር ስርዓቱን አስተዳደሩ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑን አመላክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር በስፋት ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና “በመሶብ ድሬ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫም ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን የመስጠቱን ሂደት አጠናክሮ መቀጠሉን ም/ከንቲባ ሀርቢ ገልፀው፤ የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ለአስተዳደሩ በስልጠና ጨምሮ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም አመላክተዋል።
ስርዓቱ የተንዛዛ እና ኋላቀር አሰራርን በማስቀረት ለዜጎች ፍትሃዊ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ ሲሆኑ በአስተዳደሩ የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዢ ማስጀመር በመንግስት የሚንቀሳቀሰውን ከፍተኛ ሀብት ስርዓት ውስጥ በማስገባት የአገልግሎቱን ጥራት እንደሚጨምረው ተናግረዋል።


