“የድሬዳዋን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን በኮንስትራክሽን እና በቤቶች ልማት ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ ነው” :- ኢንጂነር ዑመር ዱዓሌ የድሬዳዋ አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ

የድሬዳዋን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን በኮንስትራክሽን እና በቤቶች ልማት ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የድሬዳዋ አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዑመር ዱዓሌ ገለፁ።

ድሬዳዋ ቀደም ሲል በከተማ ፕላን ዝግጅቷ የምትታወቅና የስልጣኔ ማሳያ ተደርጋ የምትወሰድ ከተማ እንደመሆኗ መጠን፤ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉና የወደፊት የከተማዋን መስፋፋት ታሳቢ ያደረጉ የፕላን መሪዎችን (ማስተር ፕላን )ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ኢንጂነር ዑመር አያይዘውም የድሬዳዋ ታሪካዊ ቅርሶች ገጽታ ሳይነካ ህንፃዎቿንና መንገዶቿን ዳግም ዘመናዊ በሆነ መልኩ የመገንባት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ከተማዋ እያደገች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ የሚታየውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሪል ስቴት ግንባታዎች የሚከናወኑባቸው ቦታዎች መዘጋጀታቸውንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ትኩረት ተሰቶበት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ድሬዳዋ አጎራባች ሀገራትንና ቀሪውን የሀገሪቱን ክፍሎች የምታገናኝ የንግድ ማዕከል በመሆኗ በንግድና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ከተማዋ በስፋት እየሳበች እንደምትገኝ ኃላፊው አመላክተዋል።

በድሬዳዋ በ17 ሳይቶች የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተገነቡ መሆኑን ኢንጂነር ዑመር ተናግረው ያለውን ከፍተኛ የቤት ችግር ለመቅረፍ በቅርብ ቀናት ውስጥ ለ 548 ቤቶች ዕድለኞችን ለመለየት የዕጣ ማውጣት መርሃ ግብር እንደሚከናወንና ለነዋሪዎችም የማስተላለፍ ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ኢንጂነር ዑመር በመጨረሻም ቢሮው የድሬዳዋን መንገዶች ውበት ለመጠበቅ፣ ከተማዋ ለኑሮ የተመቸች እንድትሆንና የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ሳያቋርጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *