ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትህንና ማህበራዊ መስተጋብርን በማረጋገጥ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ክቡር አቶ አብዲ ሙክታር ተናገሩ።
በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት በአገር በቀል የዳኝነት እና የሽምግልና ስነ-ስርዓትን በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት ስልጠና ሰጥቷል።
በዚህም በስልጠናው መርሃ-ግብር የተገኙት የተከበሩ አቶ አብዲ ሙክታር ባህላዊ የሽምግልና ስርዓት እና ፍርድ ቤቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ግጭቶችና ችግሮች ሲፈታበት የቆየበት እሴት እና ባሕል በመሆኑን ገልፀው፤ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስርዓትንና ግጭት አፈታት እሴትን በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአስተዳደሩ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማዋቀር እና መተዳደሪያ ደንብ ለማወጣት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያብራሩት አፈጉባኤው የእነዚህ ተቋማት መኖር በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታየውን መጉላላት እና ረጅም ቀጠሮን በማስቀረት የተገልጋዩን ማህበረሰብ እርካታን ለማረጋገጥ ስለሚያሰችሉ የምክር ቤት አባላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅረበዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶቹ አሰራርና ተግባር ለሁሉም ተደራሽና ማህበረሰቡ የሚያወቀው ስነ-ስርዓትን የሚከተል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ፣ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ ናቸው።
አቶ አብዱሰላም አያይዘውም ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት መደበኛውን የፍትህ ስርዓትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚደግፈውም አመላክተዋል።


