ግምታዊ ዋጋቸው አስከ 70 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ተደረገ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ለድል ጮራ ሆስፒታል ከ50 አስከ 70 ሚሊየን ብር ዋጋቸው የሚገመት የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ተደረገ።

በድጋፍ የተበረከቱት የህክምና መሳሪያዎች የኩላሊት ማጠቢያ፣ የመተንፈሻ ማሽን፣ የልብ ማስነሻ፣ የጽኑ ህሙማን አልጋዎች እና ሌሎችም ሲሆኑ ድጋፉን ያደረገው ደግሞ መገኛውን በአውስትራሊያ ያደረገው ፉት ስክሬይ ሮተሪ ክለብ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

በህክምና መሳሪያዎቹ ድጋፍ መርሀግብር ላይ በመገኘት ርክክብ ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር አስተዳደሩ ካለበት የበጀት ውስንነት አንጻር ፉትስክሬይ ሮተሪ ክለብ ያደረገው ድጋፍ ለጤናው ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ የገቢ ምንጫቸው አነስተኛ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት ተደራሽ በማድረጉ በኩል ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።

የህክምና አገልግሎት ድንበር የማይገድበው፣ ሀይማኖትና ብሄርን ማዕቀፍ ያላደረገ እንደመሆኑ በድሬዳዋ ከአጎራባች ክልል ለመታከም የሚመጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማስተናገዱ ሂደትም የህክምና መሳሪያዎቹ ድጋፍ አስተዳደሩ ላይ የሚስተዋለውን ጫና እንደሚቀንስም ከንቲባ ከድር ተናግረዋል።

ከንቲባው በተጨማሪም ስለ ህክምና መሳሪያዎቹ ድጋፉ የፉትስክሬይ ሮተሪን በተለይ የክለቡን መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ጃማ ፋራህን አመስግነው ሌሎችም በመሠል ድጋፍ በከተማዋ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ፅጌሬዳ ክፍሌ የተደረገው የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች ድጋፍ በአይነት 41 ያህል መሆናቸውን ጠቁመው ዋጋቸውም ከ50 እስከ 70 ሚሊየን እንደሚገመት ገልጸዋል።

ዶክተር ፅጌሬዳ አክለውም የህክምና መሳሪያዎቹ ድጋፍ ተግባራዊ እንዲሆን ከአስተዳደሩ፣ ከፌዴራል እንዲሁም በግለሰብም ሆነ በተቋምና ቡድን የብዙዎች ተሳትፎ ውጤት መሆኑን አስታውሰው ድጋፉም በውጤት ረገድ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ከነበረበት ወደ ላቀ ጥራት የሚያሸጋግር እንደሆነ አመልክተዋል።

የድል ጮራ ሪፌራል ሆስፒታል ዳይሬክተር ሙና ኢብራሂም በበኩላቸው ዛሬ ከፉትስክሬይ ሮተሪ ክለብ የተደረገላቸው ድጋፍ ዘመናዊ እና አስተማማኝ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለው ድጋፉ የታለመለትን ዓላማ ከግብ እንዲደርስ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የፉትስክሬይ ሮተሪ ክለብ የህክምና መሳሪያዎቹን ድጋፉ እንዲያደርግ ያስተባበሩት በአውስትራሊያ የድሬደዋ ድጋፍ እና እርዳታ ማህበር ተወካይ አቶ ዳዊት ከበደ ለአስተዳደሩ ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለትግራይ፣ሀረሪ እና ሶማሊያ ክልል ብሎም ለጎረቤት ሀገር ጅቡቲ፣ሱዳን እንዲሁም ኬንያ መሠል ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

አቶ ዳዊት አክለውም በህክምና መሳሪያዎቹ ድጋፍ ሌሎች እንዲኖሩ ማድረግ የሚሰጠውን እርካታ እና ደስታ ያየንበት ነው ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት አጋርተዋል።

በተለይ የፈረንሳይ ሆስፒታል ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ጋር ድጋፉ ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ በመርሀግብሩ ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *