ኑሩ ኢቨንት ከድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮምሽን እንዲሁም ከድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ጋር እና ከሌሎችም አጋር አካላት ጋር በጋራ በመሆን ” ለትንሿ ኢትዮጵያ እሮጣለው”በሚል መሪ ቃል ትላንት የምሽት የተዘጋጀው የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አካሂዷል።
በመርሃ-ግብሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮምሽን ኮምሽነር ካሊድ መሀመድ እንዲሁም በአስተዳደሩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በመርሃ ግብሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተካሄደ ሲሆን ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የሩጫ ውድድሩን አስጀምረውታል።
የኑሩ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንድዬ ታደሰ የድሬን ሰላም ይበልጥ ለማረጋገጥና የኢንቨስትመንት ከተማነቷን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ የምሽት የጎዳና ላይ ሩጫ እንደ ድሬዳዋ የመጀመሪያ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድዬ የከተማዋን መልካም ስምና ገጽታ ለማስተዋወቅም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።
በሩጫው ሲሳተፉ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ድሬ ቀንም ምሽትም እንቅስቃሴ ያላት ሰላማዊ ከተማ መሆኗን ጠቁመው፤ በሩጫ ውድድሩ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
ለውድድሩ አሸናፊዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።


