የወለጋ የብልጽግና ተስፋ፤ ከታላላቅ ፕሮጀክቶች እስከ አዲስ አስተዳደራዊ ለውጥ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ለወለጋ ሕዝብ የገቡት ቃል አካባቢውን ወደ ታላቅ የኢኮኖሚ ኮሪደርነት የመቀየር ግዙፍ ራዕይ ነው።

“ሰላም ከተረጋገጠ ወለጋ ከዱባይ በላይ የመልማት ጸጋ አለው” በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል፤ ዛሬ በቢሊዮኖች ብር የሚቆጠሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር እየተቀየሩ ይገኛሉ።

ይህንን ቃል እውን ለማድረግ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ነው።

ከእነዚህም መካከል በቄለም ወለጋ ዞን ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያስተሳስረው የደምቢዶሎ-ሙጊ-ዶላ አስፋልት መንገድ ግንባታ በ1.6 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም የነቀምቴ-አንገር ጉትን-አንዶዴ መንገድ በ1.9 ቢሊዮን ብር ወጪ በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

የአየር ትራንስፖርትን ይበልጥ ለማቀላጠፍም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደምቢዶሎ የሚያደርገውን በረራ ወደ ሦስት ቀናት ያሳደገ ሲሆን፣ በነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የሥራ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው።

የአካባቢው የኢኮኖሚ ሞተር ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውና ለ50 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥረው የነቀምቴ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በ10.2 ቢሊዮን ብር በጀት መገንባቱ ሌላኛው የምሥራች ነው። ይህ ፓርክ ቡናንና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ከዚህ ጎን ለጎንም አገልግሎትን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ በኦሮሚያ ክልል ታሪክ ትልቁ የተባለው የቀበሌና የወረዳ መዋቅር መልሶ የማደራጀት ሥራ ተተግብሯል። የነቀምቴ ከተማ የኮሪደር ልማትም ከማኅበረሰቡና ከተቋማት በተገኘ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እየለማ መሆኑ ሕዝብና መንግሥት ለልማት እጅ ለእጅ መያያዛቸውን ያሳያል።

በአጠቃላይ የወለጋ ብልጽግና እውን የሚሆነው በመንግሥት የልማት ቃል እና በሕዝቡ ሰላምን የመጠበቅ ኃላፊነት ቅንጅት ሲታከልበት ነው። አሁን የሚታዩት ለውጦች አካባቢውን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ የፈነጠቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ ስትሠራ ትታያለች፤ ስትለማ ትከበራለች!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *