የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የህዝባችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱሰላም መሀመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከለውጡ አመታት በፊት ከግብር የሚገኘው ገቢ የአስተዳደሩን ወጪ ከ50 በመቶ በላይ መሸፈን የማይችል የነበረ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በአሁኑ ሰዓት ከአስተዳደሩ በሚመነጭ ገቢ የሚሰበሰበው ግብር የአስተዳደሩን ወጪ 78 በመቶ መሸፈን በመቻሉን አብራርተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የተሰበሰበው 4 ቢሊዮን ብር ያለፈው በጀት ዓመት የአንድ ሙሉ በጀት ዓመት ላይ ከተሰበሰበው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረው ይህም ድሬዳዋ ወጪዋን በራሷ የምትሸፍን ተወዳዳሪ ከተማ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።
ዶ/ር አብዱሰላም አያይዘውም ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ በተደረገው ጥረት ባለፈው አስራ አምስት ቀናት ብቻ መቶ ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ገቢዎች ባለስልጣን በግብር ከፋዩና በግብር ሰብሳቢው መተማመንን የሚፈጥሩ ስርዓቶችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ዶ/ር አብዱሰላም ጠቁመዋል።
ከነዚህም ውስጥ በዲጂታል አማራጭ ( በሞባይል ባንኪንግና በቴሌ ብር ዋሌት ) ግብርን መክፈልና የግብር ከፋዩን መረጃ በዲጂታል የማደራጀት ስራ ከማከናወን ባለፈ ግብር ከፋዩ በየወሩና ሶስት ወሩ ባለበት ሆኖ በኤስኤምኤስ(SMS) መልዕክት የግብሩን መጠን ማወቅ የሚችልበት አሰራር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ ስምምነት እየተሰጠ ለተቋሙ አቅም ለግብር ከፋዩ ደግሞ መተማመንን መፈጠሩን ተናግረዋል ፡፡


