እንቅስቃሴ የከተሞች ሕይወት ነው። አንድ ከተማ የከተማነት ሕይወት እንዲኖራት በከተማዋ ውስጥ የንግድ፣ የባህል፣ የስፖርት፣ የአስተዳደር፣ የዲፕሎማሲ፣ የእምነት፣ የኮንፈረንስ፣ ወዘተ እንቅስቃሴዎች መኖር አለባቸው። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የከተማዋን ገቢ ይጨምሩታል። ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ከተማዋን የብዙዎች መናኸሪያ እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መፍጠሪያ ያደርጓታል። የከተማዋን በጎ ገጽታም ያስተዋውቃሉ።
እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለማሣለጥ የተለያዩ የመጓጓዣ አማራጮችን በከተሞቻችን መገንባት ያስፈልጋል። ከጤናና ከመዝናኛ ጋር የተሣሠሩትን ብስክሌትን እና የእግር ጉዞን የሚያስተናግዱ መገልገያዎች እና መሠረተ ልማቶች መኖር አለባቸው። የከተማ የእንቅስቃሴ ሥፍራዎች ንቁ፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን የሚደግፉና የማኅበረሰብ ትሥሥሮችን የሚያጠናክሩ ይሆናሉ።
የብዙኃን ትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋት በተለይም የአረንጓዴ ትራንስፖርት አማራጮችን (በኤሌክትሪክ የሚሠሩትን ዓይነት) በከተማ ትራንስፖርት ሥርዓት ውስጥ በማካተት ቀልጣፋና ዘላቂ የመጓጓዣ ዘዴዎች እንዲሆኑ ማስቻል የዘመናዊነት መገለጫ ነው። ይህ አጠቃላይ የከተማ የመጓጓዣ ሥርዓት በግል መኪናዎች ላይ ያለውን ጥገኝነት ይቀንሰዋል። መጓጓዣ ለሁሉም በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን ያደርገዋል። ማኅበራዊ እኩልነትንም ለማረጋገጥ ያግዛል። ከተሞችን በሁለንተናዊ መንገድ በማልማት፣ የወደፊቱ ከተሞች የበለጸጉና የማይበገሩ እንዲሆኑ መሠረት መጣል ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው ሀገራችን የተለያዩ ምቹ የአየር ጠባይ ያሉባቸው ከተሞች ባለቤት ናት። ከተሞቻችን ከተፈጥሮ አንጻር ይህ ጎደላቸው የሚባል ነገር የለባቸውም። ከተፈጥሮ ጸጋ አንጻር ተመራጭ ሥፍራዎች ናቸው። ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ እንደ ዕድል ተጠቅመን፣ ዘመናዊነትን ለከተሞቻችን በማላበስ በዓለም ደረጃ ተመራጭ የጎብኚዎች መዳረሻ የሚሆኑ ከተሞች ባለቤት መሆን እንችላለን።
“በከተሞቻችን በመኪና ከሚጠቀመው ይለቅ እግረኛው ይበዛል። ከአዲስ አበባ ከተማ ያሉን መኪናዎች 1 ሚልዮን አይበልጡም። በቀን ውስጥ ግን ከሰባት ሚልዮን ሕዝብ በላይ በከተመዋ ይንቀሳቀሳል። ለዚህ እግረኛ የሚሆን መንገድና መቆያ ግን አይገነባለትም። በዚህ የተነሣ እግረኛው በመኪና መንገድ ውስጥ እንዲጠቀም ለእግረኞች የሚሆኑ መሠረተ ልማትና መገልገያዎች በከተሞች ውስጥ መገንባት፣ የሥልጣኔ ብቻም ሳይሆን የፍትሐዊነት ጥያቄንም የሚመልስ ነው።”
ከመደመር መንግስት
ገፅ 235


