በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንደሚገባ ተገለፀ።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተደረጉ የለውጥ ሪፎርሞች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።

በድሬዳዋ ከለውጥ ማግስት ጀምሮ የተሰሩ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የከተማዋን ገፅታ የቀየሩ ስራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ያነሱት የአስተዳደር ነዋሪዎች ድሬዳዋ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ለውጥ መምጣቱ ብሩህ ተስፋን እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዶ/ር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደሆነች የገለፁት የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪ የሆኑት አቶ ሸምሸዲን የፖለቲካ እስረኞች፣ ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች ከነበሩበት አስቃቂ የማጎሪያ ወጥተው በነፃነት የቀድሞ ስራዎቻቸውን እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡

ሌላው የአስተዳደሩ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኢልያስ መሐመድ እንዳሉት በኢትዮጲያ አሁን ያለው ሁኔታ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን የሚያሳይ ሲሆን አካታች የፖለቲካ አስተሳሰብና አደረጃጀት እንዲፈጠር ኑሯቸውን ከሃገር ውጪ በማድረግ በሃይል መንግስት ለመመስረት ዓላማ አድርገው የሚቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ሰላማዊ ትግል ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ሌላው የአስተዳደሩ ነዋሪ አቶ ክንፈ በሃገሪቱ ረጅም ጊዜ መፍትሄ ላልተገኘላቸው ጉዳዮች ምላሽ በመስጠት ሁሉን አሳታፊና እኩልነትን መርህ ያደረገ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ በማምጣት ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች በመገኘታቸው ተፎካካሪዎች ከሚኒስትርነት እስከ ታችኛው የመንግስት የስራ እርከን ገብተው በአመራርነት እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

አቶ መሀመድ ሀባስ በበኩላቸው የለውጡ መንግስት ስልጣን ላይ በወጣበት ጊዜ የተደረጉ ሪፎርሞች በኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አመላክተው ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካ ምልከታና ህዝቡን እወክላለሁ ያለ አካል ሃሳቡን እንደልቡ እንዲገልፅ አዲስ ልምምድ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ነፃና ገለልተኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲኖር መንግስት በማመቻቸቱ ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ሌላው ነዋሪ አቶ ፃድቃን ቦርዱን በአዲስ መልክ በማደራጀትና ስራዎችን በገለልተኝነት ለማከናወን የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸው የሚደንቅ ነው ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *