ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭትና ግብይት እንዲኖር ለማድረግ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥል መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ

ከወቅታዊ አለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የተፈጠረው ቀውስ ያስከተለውን ጫና ለመቀነስና መንግስት በድጎማ የሚያቀርበውን ነዳጅ ፍትሃዊና ህጋዊ በሆነ መልኩ ለማሰራጨት በአስተዳደሩ ከሚገኙ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች እና ካንፓኒዎች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በዚህም በመድረኩ የተገኙት የአስተዳደሩ ክቡር ም/ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ፣ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅን ለሚፈለገው ዓላማ ብቻ ህግን አክብረው ማሰራጨት እንደሚገባቸው እንዲሁም የንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴር እንደዚሁም የነዳጅ ኢነርጂ ባለስልጣን ያስቀመጠውን የቅድሚያ ተጠቃሚዎችን አቅጣጫ ተከትሎ ግብይቱ መካሄድ እንዳለበት በመድረኩ አስገንዝበዋል።

ቀውሱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተቀመጡትን የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት በተመለከተ የድሬዳዋ አስተዳደር በተደጋጋሚ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ማከናወኑን ያነሱት ም/ከንቲባ ሀርቢ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮቹ ማደያዎች በስነ-ምግባር ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳላቸው ገልፀዋል።

ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭትና ግብይት እንዲኖር ለማድረግ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረው የስነ-ምግባር ጉድለት የሚታይባቸው ማደያዎች ላይ እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው ወቅታዊ አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ተገን በማድረግ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ህገ-ወጥ እጥረትን የሚፈጥሩ እንዲሁም ህግን በመከተል በአግባቡ የማይሰሩና ማህበረሰቡን የማያገለግሉ ነዳጅ ማደያዎች ወደ ህጋዊ መስመር በመግባት ማህበረሰቡን በቁርጠኝነትና በስነ-ምግባር ማገልገል እንደሚገባቸው ያሳሰቡ ሲሆን በቸልተኝነት ማህበረሰቡን የማያገለግሉ ማደያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።

የነዳጅ ግብይትና ስርጭትን በሚመለከት ቀውሱ እስኪያልፍ ድረስ ልዩ ሁኔታዎች መከታተያ ክፍል ማለትም የስችዌሽን ሩም (Situation Room) ወይም «የሁኔታዎች መከታተያ ክፍል» የተዘጋጀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ንግድ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጠሃ ሲሆኑ ክፍሉ የተዋቀረው ከአስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ከፓሊስ ኮሚሽንና ከንግድ ቢሮ ጋር በጋራ በመቀናጀት መሆኑን ተናግረዋል።

ግብረ ሀይሉ በየቀኑ በመገናኘት መረጃ የሚለዋወጥ ሲሆን የስነ-ምግባር ችግሮች ከተስተዋሉ ማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፤ እንዲሁም ለፌደራል ግብረ-ሀይል መረጃ በማቀበልና በመቀበል የመተግበር ስራዎችን እንደሚሰራ አቶ አሚኖ አብራርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *