የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን በገጠር ያለውን ጥሬ ሃብት ወደ ኢንደስትሪ በመቀየር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገለፀ

የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ኢንደስትሪያላይዜሽን ሁሉን አቀፍ ልማት ስተራቴጂካዊ እምቅ አቅም ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር አካሄደ።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባ አደም የገጠር ኢንደስትራላይዜሽን በገጠር ያለውን ሰፊ የሰው ሃይል ወደ ስራ የሚያስገባ፣ ለስራ ፍለጋ የሚደረገውን ፍልሰት የሚቀንስ፤ የተመጣጠነ የገቢ ዕድገት እንዲኖር የሚያስችል እንዲሁም በየአካባቢው የሚባክነውን ጥሬ ሃብት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተሞች ብቻ በሚፈጠሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ዶ/ር ኡባ መሰረቱ የሰፋ የገጠር ኢንደስትራላይዜሽን እንዲፈጠርና ተግባራዊ እንዲደረግ ዘርፉ የሚፈልገውን ድጋፍ በማድረግ በርብርብ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች በሀብት፣ በጉልበት አቅርቦት እና በገበያ ተደራሽነት ላይ በመመስረት የክለስተሮቹን አቅም በመገምገም እና አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ንዑስ ዘርፎችን መለየት ላይ ያተኮረ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን የዕምቅ አቅም ጥናት ለማከናወን ከአስተዳደሩ የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በጋራ የመስራቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የዛሬው መድረክ ዋነኛ ዓላማ በገጠር ያለውን የኢኮኖሚ ለውጥ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የሀገር ውስጥ ሃብትና ጉልበት የሚጠቀሙ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም በድሬዳዋ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ሰነድ ማዘጋጀት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል ናቸው።

በመድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የስራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሞያዎች እንዲሁም የገጠር ወረዳዎች አመራሮች የተገኙ ሲሆን፤ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ኢንዱስትሪን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለማስፋፋት አብላጫው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚኖርበትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት እንዲሁም ሰፊ የሰው ሃይል የሚገኝባቸው የገጠር ወረዳዎች ድረስ በመውረድ የኢንዱስትሪውን መሰረት ማስፋፋት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባ አደም በገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ኢንሼቲቭ ዩኒቨርስቲው አንድ የገጠር ሞዴል ፓርክ ገንብቶ እንደሚያስረክብ ቃል ገብተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *