ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን (ሜይ ዴይ) በዛሬው እለት የሚከበር ሲሆን በዓሉ በታሪክ ሰራተኞች ለመብታቸው የታገሉበት ነው።
ዕለቱ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሞተር የሆነው ሰራተኛ ለሀገሩ እያበረከተ ያለውን የማይተካ ሚና የሚዘከርበትና የሚከበርበት ልዩ ቀን ነው።
በዚህ በዓል ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የድሬዳዋ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ሰራተኛው ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ የሥራ ስነ-ምግባርና በታማኝነት ህዝቡንና ሀገሩን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይም በመንግሥትና በግል የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሰራተኞች የሥራ ሰዓታቸውን በአግባቡ በመጠቀም፣ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት እያሳዩት ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን አመላክተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ማህበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል የውስጥ እርካታን እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
በተለይ የድሬዳዋ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ፣የንግድ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በንግድ ተቋማት ውስጥ የሚገኘው ሰራተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና አዳዲስ አሰራሮችን ከሙያ ስነ-ምግባሩ ጋር በማቀናጀት፣ የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የጀመረው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልፀዋል።
በመጨረሻም፣ ሰራተኛው ራሱን በዕውቀትና በክህሎት በማበልጸግ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን እያሳደገ እንደሚገኝና፣ ይህም ታታሪነት በምርታማነት ላይ የሚያመጣው አዎንታዊ ተፅዕኖ የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ ይበልጥ ብሩህ እያደረገው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ አመላክተዋል።


