የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በሁሉም ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለፀ

በድሬዳዋ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አባላት “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ግንቦት ወር የሚካሄደውን 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫን ምክንያት በማድረግ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በእግር ጉዞ ጨምሮ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አከናውነዋል።

በመርሃ-ግብሩ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር እንደገለጹት፣ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሴቶች በፓርቲው ውስጥ በአመራርነትና በአባላትነት ያላቸው ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ በንግድ፣ በግብርና፣ በአገልግሎትና በፈጠራ ሥራዎች ላይ የሴቶች ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልፀዋል።

ከንቲባ ከድር አያይዘው የሴቶችን የቤት ውስጥ ጫና የሚቀንሱ የአነስተኛ ማጠቢያዎችና የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታ በትኩረት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም ፓርቲው የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የሚገኙ ሴቶችን ከማገዝ ባለፈ፣ በሥራ ቅጥር ላይ ከወንዶች ጋር እኩል ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ የድጋፍ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

ፓርቲው በለውጥ ዓመታት ሴቶች በፖለቲካና በውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ደረጃ በማሳደግ ከፍተኛ ስራ የሰራ መሆኑን የገለፁት የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፤ በአስተዳደሩ በተለያዩ የአመራር የስልጣን እርከኖች ላይ ሴቶች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ በፖለቲካው ውሳኔ ላይ የሴቶች ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ከሪማ አሊ በበኩላቸው የብልፅግና ፓርቲ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም ሴቶች በየትኛውም ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲፋጠን፣ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ፍሬ እንዲያፈሩና ሰባተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ብልፅግና ፓርቲ ለሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ይህንንም ለማስቀጠል የስንዴ ነዶን መምረጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *