በነገው ዕለት በመላ ሀገሪቱ የሚከናወነውን ሰባተኛ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ያነጋገራቸው የወረዳ አንድ ነዋሪዎች ገለጹ።
የምርጫ ካርድ የበይነ-መረብ (ኦንላይን) መተግበሪያ ተጠቅመው መውሰዳቸውን የሚናገሩት የወረዳ 01 ነዋሪው አቶ ረመዳን ሰይድ፤ ለነገው ዕለት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ በመስጠት፣ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚገኘውን የመምረጥ ዕድል በጠዋት ለመጠቀም መወሰናቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው የሚገኙ ሌሎች ነዋሪዎችም ለምርጫው መዘጋጀታቸውን መታዘባቸውን የገለጹት አቶ ረመዳን፤ ምርጫው ከጅማሬው እስከ ፍጻሜው ፍጹም ሰላማዊ እንደሚሆን እምነታቸውን አጋርተዋል።
ሌላኛዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ሙኒራ ሰይድ በበኩላቸው፤ በነገው ዕለት በሚከናወነው ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ አስቀድመው መያዛቸውን ጠቅሰው፣ ነገ ማለዳ ላይ በመገኘት የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ሌሎች ያነጋገርናቸው የወረዳው ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ በአስተዳደሩ በኩል ሁሉም ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ገልጸው፤ “እኛም ነገ ከጠዋት ጀምሮ በልባችን ያሰብነውንና አገርን ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ ነን” በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል።


