የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 56ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።
የ2019 የፌዴራል መንግሥት በጀት የዐሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው የ2019-2021 የልማት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን እና የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ፣ የ2018 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎች እና ዓላማዎች እንዲሁም በመንግሥት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም እና አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮ እና ኃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
በዚሁ መሠረትም ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል 2 ትሪሊዮን 339 ቢሊዮን 268 ሚሊዮን 126 ሺህ 738 (ሁለት ትሪሊዮን፣ ሦስት መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ ሁለት መቶ ስድሳ ስምንት ሚሊዮን፣ አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺህ፣ ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት) ብር በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።


