የድሬዳዋ ወጠቶችና ስፖርት ኮሚሽን ወጣቶች እራሳቸውን ከስደተኝነት አስተሳሰብ በማላቀቅ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ምቹ የለውጥ አጋጣሚ በመጠቀም በሀገር ሰርተው በሀገር መለወጥ እንዲችሉ ግንዛቤ የሚፈጥር መድረክ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
በአስተዳደሩ 9 ቀበሌዎች እና 4 ክላስተሮች ለተውጣጡ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት በህገ ወጥ ስደት እና በኤች አይቪ ኤድስ ቀውሶች ዙሪያ የሚያተኩር ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በኮሚሽኑ የወጣቶች ማፍራት ማብቃት ቡድን መሪ አቶ መስፍን አየለ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ለህገ ወጥ ስደት በመዳረግ ህይወታቸውን እያጡ ይገኛል፡፡
ችግሩንም ለመከላከል እንዲቻል ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በማስፈለጉ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድም በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ምቹ የለውጥ የብልጽግና አስተሳሰብ በአግባቡ በመጠቀም በሀገር ሰርቶ በሀገር መለወጥ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እረገድ በአሁን ወቅት በወጣቱ ላይ የሚስተዋለውን መዘናጋት ለማስቀረትም መድረኩ ዓላማ ማድረጉን አቶ መስፍን አየለ ተናግረዋል፡፡
በኮሚሽኑ የወጣቶች ተሳትፎና ክትትል ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሳህሉ አምባይ ይህ ህገ ወጥ ስደት እና በኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ላይ ያተኮረ መድረክ በዋነኝነት ወጣቶችንም ሆነ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የችግሩን መጠን ለመቀነስ ግንዛቤውን ወደታች ለማውረድ ዓላማን አንግቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን መሰል እና ተያያዥ ችግሮች ለመከላከል በየቀበሌው የድጋፍና ክትትል ባለሞያዎችን በማሰማራት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መድረኩ ለቀጣይ አንድ ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን በከተማ ከዘጠኙም ቀበሌዎች እንዲሁም በገጠር ከ4 ክላስተሮች በድምሩ ከ800 በላይ ወጣቶች እና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ይሆናሉ


