የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የህብረተሰቡ በልማት ስራ መሳተፍ የጎላ ሚና እንዳላቸው ተገለፀ ::

    የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት ቢሮ በአስተዳደሩ ከተማ ቀበሌዎች ቀደም ባሉት አመታት የህብረተሰብ ተሳትፎ እና የልማት የመንደር ኮሚቴ የነበሩ ሲሆን በግጭትና በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የልማት ስራ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሁለት ተከታታይ ቀናት መክረዋል፡፡
    ድሬደዋን በመሰረተ ልማት የተሻለች እና ፅዳቷን የጠበቀች ሞዴል ከተማ እንድትሆን ማህበረሰቡና መንግስት በቅንጀት መስራት ይኖርባቸዋል ያሉት የአስተዳደሩ የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ጀማል ኢብራሂም እንደተናገሩት በቀጣይ 10 አመት የብልፅግና መሪ እቅድ የያዝንበት አመት በመሆኑ ለዚህ አፈፃፀም የሚጠቅም አደረጃጀት ሊኖር ይገባል ብለዋል ፡፡
    ኢንጂነር ጀማል ከዚህም ጋር አያይዘው ቀደም ባሉት አመታት በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በልማት የመንደር ኮሚቴ በሚሰሩ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡ ድርሻ 50 በመቶ የመንግስት ድርሻ 50 በመቶ ሆኖ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተከናውነዋል በማለት ባለፉት ሁለት አመታት በነበረ አለመረጋጋትና የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በቀጣይ ጊዜያት በሚከናወኑ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ 30 በመቶ የመንግስት ተሳትፎ 70 በመቶ እንዲሆን መወሰኑንም ጠቁመዋል ፡፡
    በማህበረሰብ ተሳትፎ እና የልማት የመንደር ኮሚቴ በመደራጀት በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን የፀጥታ ችግር ማህበረሰቡ ተቀራርቦ እንዲሰሩ ስለሚያደርግ የልማትቱ ሃይል እንዲሆኑ ይረዳልም ብለዋል፡፡
    የህብረተሰብ ተሳትፎ ልማት ኤጀንሲ ዳይሬቶሪት ዳይሬክተር አቶ ጎንፋ ሞሲሳ በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት ቀደም ሲል የነበረውን እቅድ በመከለስ ህብረተሰቡ በወቅታዊ ችግር የጠፉ ንብረቶችንና አዲስ በእቅድ የተያዙ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በመስራት ህብረተሰቡን እና መንግስትን የማቀራረብ ስራዎችን ለመስራት በውይይቱ የተሳተፉ ተሳታፊዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
    በልማት ስራው ህብረተሰቡ በጉልበትና በገንዘባቸው የሚያሳዩት ፍቃደኝነት ለልማት ስራው ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው በማለት ወደስራ ሲገባም ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር በአስተዳደሩ በመሀበር ለተደራጁ ማህበርት ቅድሚያ እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል፡፡
    በውይይቱ የተሳተፉ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት በልማት ስራው የድርሻቸውን በመወጣት በአካባቢያቸው ያለውን የመንገድ ዳር መብራት ችግር ፣የውስጥ ለውስጥ የኮብልስቶን መንገዶችን፣ የጎርፍ ማስኬጃ ቦዮች እንዲሁም የአረጋዊያን ቤት የመጠገን ስራዎች ቅድሚያ በመስጠት እነደሚንቀሳቀሱም ገልፀዋል፡፡