በቀጣይ 5 ዓመት በአስተዳደሩ በገጠርና በከተማ የሚገነቡ ቤቶች አስመልክቶ የአስተዳደሩ ከንቲባና ከፍተኛ አመራሮች በቤቶች ልማት ጥናቶች የግምገማ እና የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የቤት አቅርቦት ስትራቴጂ ፍሬምዎርክ ጥናት ሰነድ ፣ የወጪ ቆጣቢና አዋጪ የቤት ልማት ዲዛይን ጥናት ሰነድ ፣ የገጠር ቤት ዲዛይን ሰነድ የቀረቡ ሲሆን አመራሩ በስፋት ተወያይተውባቸዋል፡፡
የአስተዳደሩ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም ለቀጣይ 10 ዓመታት በሀገራችን የተጀመረውን የብልጽግና ፍኖተ ካርታ መሪ እቅድ 4.4 ሚሊዮን ቤቶች እንደ ሀገር በመንግስት አስተባባሪነት ለመገንባት መታሰቡን በመጠቆም እንደ አስተዳደር ይህንን እቅድ ለማሳካትና የቤት ጥያቄን ትኩረት ሰጥተን ለመመለስ በቀጣይ 5 ዓመታት 50 ሺህ ቤቶች ለመገንባት የብድር ምችችት ከፌደራል በመፈቀዱ እየተጠባበቅን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ኢንጂነር ጀማል ከዚህ ጋር በማያያዝ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ወደ ተግባር በመግባት በዘንድሮ ዓመት 13 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የመሬት አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ ግንባታ ለመገንባት ቀደም ሲል የነበሩትን G+3ወደ G+10ለማድረስ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
ድሬዳዋ የተሻለች ከተማና ለኑሮ አመቺ ከተማ እንድትሆን አስተዳደሩ የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ህብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ የእድሉን ተጠቃሚ እንዲሆን እንጂነር ጀማል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ማጠቃለያ የአስተዳደሩ ከንቲባ አህመድ መሀመድ ቡህ እንደተናገሩት በአስተዳደሩ ያሉ ቤቶች በብዛት የፈረሱ በመሆናቸው ማንም ሰው ከቦታው ሳይፈናቀል ያሉትን ክፍት መሬቶችን በመጠቀም ለኑሮ ምቹ የሆኑ ቤቶችን መገንባት ይኖርብናል ብለዋል።
ከንቲባው ከዚህም ጋር በማያያዝ በአስተዳደሩ ቁልፍ የሆነውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በዕቅድ የተያዘውን እቅድ በማሳካት ድሬደዋ ካለፉት 27 አመታት በፊት የነበራትን ውበቷን ለመመለስ አመራሩ የላቀ ቁርጠኝነት ይዞ አፈፃፀሙ እንዲሳካና ውጤት ለማስመዝገብ ተግቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።


